ዩክሬን የእህል ምርቷን በባቡር ወደ አውሮፓ ሀገራት ለመላክ አቅዳለች
ሩሲያ ከ”ጥቁር ባህር የእህል ስምምነት” መውጣቷን ተከትሎ ነው ኬቭ የግብርና ምርቷን በባቡር ለማጓጓዝ የወጠነችው
በሞስኮ ከስምምነቱ መውጣት ከዩክሬን ስንዴ እና ማዳባሪያ በስፋት የሚያስገቡ ሀገራት ይጎዳሉ ተብሏል
ዩክሬን የእህል ምርቷን በባቡር ወደ አውሮፓ ሀገራት ለማስገባትና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየሰራች መሆኑ ተገልጿል።
ኬቭ ስንዴ እና ማዳበሪያ በባቡር ለመጫንና ወደ ውጭ ለመላክ ያሰበችው ሩሲያ ትናንት ከ”ጥቁር ባህር የእህል ስምምነት” (በመርከቦች ምርቶቹን ማስወጣት የሚያስችል) በመውጣቷ ነው።
ሞስኮ የምዕራባውያኑ ማዕቀብ እንዲላላ ያስቀመጠችው ቅድመ ሁኔታ አለመመለሱን በመጥቀስ ከስምምነቱ ወጥታለች።
በመንግስታቱ ድርጅት እና ቱርክ አደራዳሪነት የተደረሰው ስምምነት እንደ ኦዴሳ ባሉ ወደቦች የተከማቸ ከ33 ሚሊየን ቶን በላይ እህል ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ እድል ፈጥሯል።
ሩሲያ ከዚህ ስምምነት መውጣቷን ማሳወቋ በተለይ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራትን እጅጉን እንደሚጎዳ ነው የተገለጸው።
“ውሳኔው የዋጋ ንረትን የሚያስከትልና አጠቃላይ ገበያውን የሚረብሽ ነው” ብለዋል በአረብ ኤምሬትስ የዩክሬን አምባሳደር ዲሚትሮ ሴኒክ።
አምባሳደሩ ሀገራቸው በአለማቀፍ ደረጃ የምግብ ዋስትና ቀውስ እንዳይፈጠር አማራጮችን እየፈለገች መሆኑን ነው ለዘናሽናል የገለጹት።
ኬቭ የወደቦቿን ጭነት የማስተናገድ አቅም ከማሳደግ ባሻገር በባቡር እና በመኪና ምርቶቿን ወደ አውሮፓ ሀገራት ለመላክ እየተንቀሳቀሰች መሆኑንም አብራርተዋል።
በፖላንድ እና ሮማኒያ በኩል ምርቶችን ለአለም ገበያ የማቅረቡ ሂደት ግን ጊዜ መውሰዱ እንደማይቀር አልሸሸጉም።
ዩክሬን ወደ ጥቁር ባህር ወደቦቿ በማቅናት እህል ለሚጭኑ የንግድ መርከቦች 547 ሚሊየን ዶላር የኢንሹራንስ ፈንድ ይፋ ማድረጓንም ነው አምባሳደር ሴኒክ የገለጹት።
የንግድ መርከቦቹ በሞስኮ ጥቃት ቢመቱ ካሳ እንደሚከፈላቸው ቃል ስለተገባላቸው የተለያዩ ኩባንያዎች ከኬቭ ጋር ለመስራት ፍላጎት አሳይተዋልም ብለዋል።
በስንዴ፣ ገብስ፣ ሰሊጥ፣ በቆሎ እና ማዳበሪያ ምርቷ ከአለማችን ቀዳሚ ሀገራት የምትጠቀሰው ዩክሬን ባለፈው አመት ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ስትገባ የአለም የምግብ ዋጋ መናሩ ይታወሳል።
በ38 ሀገራት ከ40 ሚሊየን በላይ ሰዎች ለረሃብ መጋለጣቸውን የሚገልጸው የመንግስታቱ ድርጅትም የጦርነቱ መቀጠል እና የሩሲያ ከ”ጥቁር ባህር የእህል ስምምነት” መውጣት ቀውሱን ያባብሰዋል ብሏል።