አብንን ጨምሮ የተለያዩ ፓርቲዎች ውሳኔው እንዲሰረዝና ሰላምና መረጋጋት የሚያመጡ ንግግሮች እንዲደረጉ ጠይቀዋል
በጎንደር ከተማ የስራ እላፊን ጨምሮ የተለያዩ ክልከላዎች ተላለፉ።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ኮማንድ ፖስት ሚያዝያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ነው ክልከላዎችን ያሳለፈው፡፡
ክልከላዎቹ በከተማዋ ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችሉ ታምኖባቸዋል።
ኮማንድ ፖስቱ ከዚህ በታች የተጠቀሱት የተከለከሉ ናቸው ብሏል፦
1 . በከተማው ያሉ ማንኛውም መጠጥ ቤቶችና ጭፈራ ቤቶች ከምሽቱ 3 ሰዓት በኋላ አገልግሎት መስጠት፣
2 . በከተማው የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባለ 3 እግር ባጃጆች ከንጋቱ 12:00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2:00 ሰዓት ውጭ መንቀሳቀስ፣
3 .ከተፈቀደለት የመንግስት የፀጥታ ኃይል ውጭ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ፣
4 . ድምፅ አልባ መሳሪያዎችን ስለታማ የሆኑ እንደ ጩቤ ፣ ገጀራ ፣ አንካሴ ፣ ጦርና ፌሮ ብረት ወዘተ የመሳሰሉትን ይዞ መንቀሳቀስ፣
5 . በህግ የሚፈለጉ ወይም ተጠርጣሪዎችን ሽፋን መስጠት፣ መደበቅ፣ መረጃ ሰጥቶ ማስመለጥ፣ የፀጥታ ሃይሎችን የህግ ማስከበር ተልዕኮ ማደናቀፍ ማወክ፣
6. በማንኛውም ቦታና ስዓት ጥይትም ሆነ ሮኬት ርችት መተኮስ፣
7. በተከለከሉ ቦታዎች በእምነት ተቋማት፣ በገበያዎች፣ ህዝብ በብዛት በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ፣ በሆቴሎች፣ መጠጥ ቤቶችና ግሮሰሪዎች፣ ልዩ ልዩ መዝናኛ ቦታዎች ጦር መሳሪያ ይዞ መገኘትና መንቀሳቀስ፣
8 . የሠራዊቱን ሚሊተሪ (አልባሳት) ከሰራዊቱ አባላት ውጭ መልበስ፣ የልዩ ኋይል፣ የፖሊስ ፣ የመከላከያ ሠራዊት ፣ የፌዴራል ፖሊስ መልበስ፣
9 . ከመንግስት እውቅና ውጭ ስብሰባ ማድረግ፣ ወታደራዊ ስልጠና መስጠት፣
10. አድማ መቀስቀስ፣ ማድረግና ማስተባበር እንዲሁም መደበኛ ስራን ማስተጓጎል፣
11 . ፀጉረ ልውጥ/አጠራጣሪ ሰው ከቤቱ ያሳደረ፣ ያከራየ፣ በሆቴሉ አልጋ ያስያዘ እንዲሁም ለሚመለከተው የፀጥታ አካል ጥቆማ ያልሰጠ በህግ ይጠየቃል ብሏል ኮማንድ ፖስቱ።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ኮማንድ ፖስት ክልከላዎቹን ያወጣው ከልዩ ሃይል አደረጃጀቶች መፍረስ ጋር በተያያዘ ተቃውሞዎች በበረቱበት ወቅት ነው።
ጎንደርን ጨምሮ በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች የልዩ ሃይል አደረጃጀቱን ማፍረስ ትጥቅ ከማስፈታት ጋር የተያያዘ ነው የሚሉ የተቃውሞ ስልፎች ተደርገዋል።
በሰሜን ወሎ ዞን የተለያዩ ከተሞች የትራንስፖርት፣ ቴሌኮም እና ሌሎች አገልግሎቶች መቆራረጥ እየተስተዋለ እንደሚገኝም ነው አል ዐይን ከአይን እማኞች የሰማው።
መንግስት ግን የልዩ ሃይል አደረጃጀቱን የማፍረስ ውሳኔውን “ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን” ከመፈጸም እንደማይመለስ ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ትናንት ባወጡት መግለጫ፥ "ይህ ውሳኔ በሁሉም ክልል አመራሮች በጋራ የተወሰነና በጋራ የሚተገበር ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
የክልሎች ፉክክር በልዩ ኃይል ፖሊስ ግንባታ ሳይሆን በልማት ሊሆን እንደሚገባም ነው በመግለጫቸው ያሳሰቡት።
አብንን ጨምሮ የተለያዩ ፓርቲዎች ባወጧቸው መግለጫዎች ግን ውሳኔው እንዲጤንና ሰላምና መረጋጋት የሚያመጡ ንግግሮች እንዲደረጉ ጠይቀዋል።