የተደረሰው ውሳኔ "ለሕብረ ብሄራዊ አንድነት" ሲባል እንደሚተገበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገለጹ
በውሳኔው ላይ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፖርቲዎች የተለየ አተያይ አላቸው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ከዚህ በኋላ ክልሎች የፖሊስ ኃይላቸውን አጠናክረው ወንጀልን በመከላከልና አካባቢያዊ ጸጥታን በማስከበር ላይ ብቻ ያተኩራሉ" ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በክልሎች ያሉ የልዩ ኃይል አደረጃጀቶች እንዲፈርሱ የተደረሰው ውሳኔ "ለአንድነትና ለህዝብ ሰላም ለማስጠበቅ ሲባል ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን" እንደሚተገበር ገልጸዋል።
- የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ እንቅስቃሴ ማካሄድ መጀመሩን መንግስት አስታወቀ
- ከሰሞኑ መንግስትልዩ ኃይል እንዲፈርስ መወሰኑን ተከትሎ በአማራ ክልል ተቃውሞ ተቀሰቀሰ
የክልል ልዩ ኃይሎች እንዲፈርሱ መወሰኑን ተከትሎ በተለይም በአማራ ክልል ተቃውሞ ተነስቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ ወይም ወደ ክልል ፖሊስ ሰራዊት እንዲካተቱ ውሳኔ ሲደረግ ተገቢ ዝግጅት ተደርጎበት ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉዳዩ የትጥቅ መፍታት ሳይሆን የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት ተገቢ ስልጠናና ትጥቅ ወደሚያገኙበት እና ሀገርን በተሻለ ሁኔታ ወደሚያገለግሉበት መዋቅሮች ማስገባት እንደሆነ ገልጸዋል።
"ይህ ውሳኔ በሁሉም ክልል አመራሮች በጋራ የተወሰነና በጋራ የሚተገበር ነው። አብዛኞቹ ክልሎችም ሠራዊት ለማስተዳደር የሚያስችል የኢኮኖሚ ዐቅም የላቸውም። ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ በፌዴራል መንግሥት ከሚሰጣቸው በጀት ለልዩ ኃይላቸው የሚጠቀሙ ናቸው።" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የክልሎች ፋክክር በልዩ ኃይል ፖሊስ ግንባታ ሳይሆን በልማት ሊሆን ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ከዚህ በኋላ ክልሎች የፖሊስ ኃይላቸውን አጠናክረው ወንጀልን በመከላከልና አካባቢያዊ ጸጥታን በማስከበር ላይ ብቻ ያተኩራሉ" ብለዋል።
የሀገርን ድንበር እና ሉአላዊነትን የሚገዳደር ኃይል ሰኖር መከላከያ ሰራዊት እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል መንግስትም በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ የልዩ ኃይሎች ላይ የተደረሠው ወሳኔ ተገቢ መሆኑን አና ከልዩ ኃይል ፖሊሶች እና ከህዝብ ጋር እንደሚመክርበት ገልጿል።
በውሳኔው ላይ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፖርቲዎች የተለየ አተያይ አላቸው።
መንግስት የልዩ ኃይል አደረጃጀትን እንዲፈርስ ያሳለፈውን ውሳኔ ወቅቱን የጠበቀ አለመሆኑን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የኢትዮጵያ ለማህበራዊ እና ለፍትህ ፖርቲ ( ኢዜማ) ተቃውመውታል።
መንግስት ልዩ ሀይሉን "የጋራ መግባባት እና መተማመን" ሳይደረስ ለማፍረስ መወሰኑ ኃላፊነት የጎደለው ነው ሲል በጽኑ ተቃውሟል አብን።
በፌደራል መንግስት የጸጥታ ኃይሎችና በክልሉ ልዩ ኃይል መካከል ውጥረት መንገሱን የገለጸው አብን መንግስት ውሳኔውን እንዲቀለብስ ጠይቋል።
"ቀጥተኛ እና ተገማች ጥቃት ያለባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች" በመኖራቸው ውሳኔውን እንደማይቀበለው የገለጸው አብን ውሳኔ ከክልሉ አልፎ በሀገር ደረጃ አለመረጋጋት የሚፈጥር ነው ብሏል።
ኢዜማ ህወሓት "በአማራ ክልል ስር ያሉ አካባቢዎችን" አስመልሳለሁ እያለ ባለበት ወቅት የመንግስት "በጥድፊያ እና በድብቅ" ወደ ተግባር መግባት ወቅታዊ አይደለም፤ውጤቱም አደገኛ ነው ብሏል።
ከሁለት አመት በፊት በትግራይ ክልል ተጀምሮ አማራ እና አፋር ክልሎችን ያዳረሰው ጦርነት መጠነ ሰፊ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ካደረሰ በኋላ የፌደራል መንግስቱ እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ በደረሱት ስምምነት መቆሙ ይታወሳል።
በትግራይ እና በአማራ ክልል ያሉ የማንነት እና የወሰን ጥያቄ ያለባቸው አካባቢዎች ድጋሚ የግጭት መንሰኤ ይሆናሉ የሚል ስጋት አለ።