ጎግል ማስታወቂያዎችን የሚያስተዳድርበት መተግበሪያውን እንዲሸጥ ተጠይቋል
የአልፋቤት ንብረት የሆነው ጎግል በአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር ክስ ቀርቦበታል።
ኩባንያው የዲጂታል ማስታዎቂያዎችን በበላይነት ይዞ ኢፍትሃዊ ፉክክርም እያደረገ ይገኛል የሚል ክስ ነው የቀረበበት።
የሚከተላቸው ስትራቴጂዎችም የአንድ ፈረስ ጉዞን ብቻ የሚፈቅዱ ናቸው ይላል ክሱ።
የጎግል ፍትሃዊ ያልሆነ ፉክክር እንደ አማዞን፣ ሜታ እና አፕል ያሉ ኩባንያዎችን እየጎዳ መሆኑንም በቨርጂኒያ አካባቢ ፍርድ ቤት ክስ ያመላክታል።
የባይደን አስተዳደር ከዚህ ቀደምም ጎግል ህገወጥ የሆነና ተፎካካሪዎቹን ከገበያ የሚያስወጣ ተግባሩን እንዲያቆም ማሳሰቡን ሬውተርስ አስታውሷል።
ጎግል በ2021 ከ12 በመቶ በላይ ገቢ ያስገኘለትን የማስታወቂያዎች ማስተዳደሪያ ወይም መተግበሪያውን እንዲሸጥም ተጠይቋል።
ከጠቅላላ ገቢው 80 ከመቶውን ከማስታወቂያዎች የሚያገኘው ጎግል ግን ክሱን መሰረተ ቢስ ነው ብሎታል።
"ፈጣራን አያበረታታም፣ የማስታወቂያ ወጪንም እንዳሻው እያናረ ነው" የሚለውን ክስም ውድቅ አድርጓል።
"ኩባንያው የሚከተለው ኢፍትሃዊ ስትራቴጂ አነስተኛ የቢዝነስ ተቋማት እንዳያድጉ ያደርጋል" በሚል የተነሳበትን ክስም አጣጥሎታል።
ጎግል በድረገፆች ላይ ማስታዎቂያዎችን የሚያስተናግድበትና የገቢ ክፍፍሉም ጥያቄ እየተነሳበት ነው።
የጎግል መቀመጫዋን ካሊፎርኒያ ጨምሮ ስምንት የአሜሪካ ግዛቶች በኩባንያው ላይ የተከፈተውን ክስ እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።