“የምጽአት ቀን ስአት” ስለኒዩክሌር ጦርነት መቃረብ ምን ይላል?
የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “የምጽአት ቀን ስአት” ለኒዩክሌር ጦርነት ጅማሮ ሁለት ደቂቃ መቅረቱን ያመላክታል ብለዋል
“የምጽአት ቀን ስአት” ከ1947 ጀምሮ አለማችን የተደቀነባትን አደጋ በልዩ መንገድ እየቆጠረ ስጋቶችን ያሳያል
ሩሲያ የኒዩክሌር ጦርነት እየተቃረበ መምጣቱን ገለጸች።
የሀገሪቱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ሪያብኮቭ የ”ምጽአት ቀን ስአት” የኒዩክሌር ጦርነት መቃረቡን አመላክቷል ብለዋል።
“ስአቱ ለምጽአት ቀን እኩለ ሌሊት ሁለት ደቂቃዎች መቅረቱን አሳይቷል፤ ይህ ግን የኒዩክሌር ጦርነት አይቀሬ መሆኑን አያመላክትም” ነው ያሉት ሪያብኮቭ።
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከአሜሪካ ጋር ባለፈው አመት ከባድ ውጥረት ውስጥ ስትገባ የ”ምጽአት ቀን ስአቱ” ለምጽአት እኩለ ሌሊት (የኒዩክሌር ጦርነት ጅማሮ) 90 ሰከንዶች ቀርተዋል ሲል ማመላከቱ ይታወሳል።
ይህ ስአት በዚህ አመት ለምጽአት እኩለ ሌሊት ሁለት ደቂቃዎች ቀርተዋል በሚል የኒዩክሌር ጦርነት የመጀመር እድሉን ካለፈው አመት በ30 ሰከንዶች ወደኋላ ቢያስቀረውም ጦርነቱ ግን ይቀራል ማለት አይደለም ብለዋል የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር።
የ”ምጽአት ቀን ስአት” በፈረንጆቹ 1947 ነው ተመርቆ አለማችን የተደቀነባትን የመጥፋት አደጋ መቁጠር የጀመረው።
አቆጣጠሩ ከመደበኛዎቹ ስአቶች የሚለየው የ”ምጽአት ቀን ስአት” አለም በሰው ሰራሽ ወይንም በተፈጥሮ አደጋ ልትጠፋ የምትችልበትን ጊዜ በልዩ መንገድ ይቆጥራል።
ሃሳባዊ የምጽአት እኩለ ሌሊት አስቀምጦም የኒዩክሌር ጦርነትም ሆነ ሌሎች አለምን ሊያወድሙ የሚችሉ አደጋዎች ለመጥፊያዋ ጊዜ (የምጽአት እኩለ ሌሊት) የቀሩ ደቂቃና ሰከንዶችን ይቆጥራል።
የኖቬል ተሸላሚዎችን አባል ያደረገ አለማቀፍ የባለሙያዎች ቡድንም ስአቱን በየአመቱ ይሞሉታል።
አለማቀፍ ውጥረት ሲባባስ የምጽአት ቀን ስአቱ በፍጥነት እየቆጠረ ለመጨረሻዋ ሌሊት መቃረብን ያመላክታል።
አንዳንዶቹ የስአቱ ፋይዳ ብዙ ባይዋጥላቸውም ባለሙያዎች ግን አለማችን የተጋረጠባትን አደጋ ስለሚጠቁምና ስለሚያስጠነቅቅ በቀላሉ ሊታይ አይገባም ይላሉ።
ሩሲያም የኒዩክሌር ጦርነት ለሚጀመርባት ሌሊት 2 ደቂቃዎች ቀርተዋል ሲል ያመላከተውን ሰአት መረጃ በመመርኮዝ ጦሯ ዝግጁ እንዲሆን አዛለች።
ምዕራባውያን በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት የሚያደርጉት ጣልቃገብነት የኒዩክሌር ጦርነትን ያስነሳል በሚል ደጋግመው ያሳሰቡት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፥ ሀገራቸው አሜሪካን መምታት የሚችሉ ሚሳኤሎች እንዳሏት መናገራቸው ይታወሳል።
አሜሪካ በ2026 ወደ ጀርመን ረጅም ርቀት የሚምዘገዘጉ ሚሳኤሎችን የምትልክ ከሆነም የኒዩክሌር ጦርነቱ አይቀሬ መሆኑን የሚጠቁም መግለጫ በቅርቡ መስጠታቸው አይዘነጋም።