“ሰብዓዊ ድጋፍ የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ድጋፉን እንዲያገኝ ማድረግ ከየትኛውም ነገር በላይ ቅድሚያ የምሰጠው ጉዳይ ነው”-ማርቲን ግሪፊትስ
“ግጭቱ እንዲቆም እንፈልጋለን”ም ብለዋል የሰብአዊ ጉዳዮች ኃላፊና የአስቸኳይ እርዳታ አስተባባሪው
ግሪፊትስ በትግራይ የተመለከትቱት ነገር “ልብን የሚሰብር ነው” ብለዋል
“በትግራይ ይሁን በአማራ፣ በአፋር በየትኛውም የሃገሪቱ አካባቢ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ድጋፉን እንዲያገኝ ማድረግ ከየትኛውም ነገር በላይ ቅድሚያ የምሰጠው ጉዳይ ነው” ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊና የአስቸኳይ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ ገለጹ፡፡
ኃላፊው ላለፉት 6 ቀናት በኢትዮጵያ የነበራቸውን ቆይታ በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ግሪፊትስ በቆይታቸው ከጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ከም/ጠ/ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና ከሰላም ሚኒስትሯ ሙፈርያት ካሚል እንዲሁም ከተለያዩ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ አፍሪካ ህብረት ፣ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ እንዲሁም የተለያዩ የሰብዓዊ እርዳታ እና ለጋሽ ድርጅቶች ከወከሉ አካላት ጋር ተወያይተዋል፡፡
በትግራይ ክልል የሁለት ቀን ቆይታ እንደነበራቸው የገለጹት አስተባባሪው በግጭት ምክንያት በክልሉ አሳዛኝ ነገር መከሰቱንና ከባድ የሰብዓዊ ሁኔታ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
“ቤታቸውንና እርሻቸውን ጥለው ከመንደራቸው ወይም ከተሞቻቸው መሰደዳቸውን ተከትሎ ያላቸውን ሁሉ ካጡ የትግራይ ሰዎች ጋር ተገናኝቻለሁ። በሀውዜን ቤታቸው ተቃጥሎ ሰብላቸው የተዘረፈ ቤተሰብ ጎብኝቻለሁ። እስከ ዛሬ ድረስ የመኖሪያ ቦታም ሆነ የሚያስቀምጡትን ምግብ የሌላቸው ቤተሰቦች ማየት ለኔ ልብን የሚሰብር ነበር ” በማለትም ነበር የችግሩ አስከፊነት የገለጹት የኦቻ ኃላፊው ግሪፊትስ፡፡
ግሪፊትስ በትግራይ ክልል አሰቃቂ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች እና ተደፍረዋል የተባሉ ሴቶች ማግኘታቸው እንዲሁም በስልት ሆን ተብለው እንዲወድሙ የተደረጉ ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን፣ የውሃ ፕሮጀክቶች እና የሲቪል መሠረተ ልማቶችን መመልከታቸውንም አስታውቀዋል፡፡
የጤና ተቋማት በመውደማቸው የጥቃቱ ሰለባዎች ተገቢ ህክምና ለማግኘት የማይችሉበት ሁኔታ እንዳለም ተናግረዋል ኃላፊው፡፡
በክልሉ የቴሌኮሚዩኒኬሽን እና ባንክ አገልግሎት እንዲሁም የነዳጅ አቅርቦት አለመኖሩ ያለውን የሰብዓዊ ሁኔታ እንዳከበደውም ነው የገለጹት፡፡
በተለይ በትግራይ የተጀመረው ግጭት አሁን ላይ ወደ አማራ እና ዓፋር ክልሎች መስፋፋቱ የሚያስፈልገው የሰብዓዊ እርዳታ መጠኑን ከፍ አድርጎታል ብለዋል፡፡
“ዘገምተኛ የዕርዳታ እንቅስቃሴ እንዲኖር ምክንያት የሆኑትን ሁኔታዎች መለወጥ አለብን - ግጭቱ እንዲቆም እንፈልጋለን” ሲሉም ነው የተደመጡት ግሪፊትስ፡፡
ከትግራይ በተጨማሪ የሰብዓዊ እርዳታ ሰጪ ተቋማት በሚልዮን ለሚቆጠሩና በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እያደረጉ ነው ያሉት ግሪፊትስ አሁን ላይ “ለትግራይ፣ ለአማራም ሆነ ለአፋር ክልሎች የሚያፈልገውን ሰብዓዊ እርዳታ ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡