በትግራይ ከሕግ ማስከበር ዘመቻ ወዲህ ለ1.8 ሚ. ሰዎች ሰብዓዊ ድጋፍ መድረሱን የሰላም ሚ/ር ገለጸ
ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተካተቱበት የአስቸኳይ ጊዜ ኦፕሬሽን ማስተባበሪያ ማዕከል በመቀሌ ተቋቁሟል
በክልሉ 2.5 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል
በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ሂደት ከተጠናቀቀ ወዲህ ምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችና የህክምና አቅርቦቶችን የያዘ የሰብዓዊ ድጋፍ በትግራይ ክልል ለሚገኙ 1.8 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች መድረሱን የሰላም ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በክልሉ 2.5 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው።
ሚኒስቴሩ እንዳለው በአስቸካይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል (ኢ.ሲ.ሲ) የሚኒስትሮች ኮሚቴ መሪነት አፋጣኝ ፍላጎቶችን ለማሟላት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ከክልል ቢሮዎች፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅቶችና ከዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተውጣጡ የቴክኒክ ቡድኖችን ያካተተ የአስቸኳይ ጊዜ ኦፕሬሽን ማስተባበሪያ ማዕከል (ኢ.ኦ.ሲ) በመቀሌ ከተማ ተቋቁሟል።
ተጨማሪ ፍላጎቶችን ለመለየት ባለ አራት ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበር ስርዓት (የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የምግብ ማከፋፈያ ቦታዎቸን ያካተተ) ተደራጅቶ ወደ ሥራ መገባቱንም መግለጫው አንስቷል፡፡
ተለይተው ለታወቁ ተጠቃሚዎች የድጋፍ ሽፋን ለማድረግ እንዲሁም በፍጥነት አቅርቦትን ለማዳረስ የኢትዮጵያ መንግስት ከልማትና ሰብዓዊ አጋሮች ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ መሆኑን ሚኒስቴሩ ይፋ አድርጓል።
ብሔራዊ የመከላከያ ሰራዊት ደህንነቱ የተጠበቀ የሰዎችና የአቅርቦቶች እንቅስቃሴን በማመቻቸት የሰብዓዊ እርዳታውን ቅንጅት በከፍተኛ ደረጃ በመደገፍ ላይ እንደሚገኝም ሚኒስቴሩ በመግለጫው ጠቅሷል።
ስርጭቱ በብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ (ዩ.ኤን.ኦቻ) አስተባባሪነት በዓለም አቀፍና በሀገር በቀል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም በሴፍቲኔት መርሃ ግብር (ፒ.ኤስ.ኤን.ፒ) እየተከናወነ መሆኑንም መግለጫው ያትታል።
ስርጭቱ የሚከናወነው በአክሱም፣ አዲግራት፣ አላማጣ ፣ መቀሌ ዙሪያ፣ ሽሬና መቀሌ ከሚገኙ የማሰራጫ ጣቢያዎች እንደሆነም ነው የተገለጸው።
በስርጭት ሂደቱ ለሴቶች፣ ህጻናት፣ አረጋውያንና የአካል ጉዳተኞች ለምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁስና የህክምና አቅርቦቶች ስርጭት ቅድሚያ እየተሰጠ ይገኛል ተብሏል።
መንግስትና ሰብዓዊ አጋሮች እ.ኤ.አ. ህዳር 29 ቀን 2020 በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት መሰረት በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙ የጠቀሰው መግለጫው፣ የተጠቃሚዎችን ብዛት በትክክል ለመለየት የጋራ የፍላጎት ዳሰሳና ግምገማ እየተካሔደ እንደሚገኝም ገልጿል።
ቀድሞም ከ1.6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የዕለት ደራሽ በሚፈልጉበት የትግራይ ክልል፣ በሕወሓት ኃይል እና በፌዴራል መንግስት መከላከያ ሠራዊት መካከል ከተደረገው ውጊያ በኋላ ችግሩ ተባብሷል፡፡