በሱማሌ ክልል በተከሰተ አዲስ በሽታ ሰዎች እየሞቱ ነው መባሉን መንግስት አስተባበለ
በሽታውን የተመለከቱ አጠቃላይ መረጃዎችን በቀጣዩ ሳምንት ይፋ እንደሚያደርግም ገልጿል
ነዳጅ በሚወጣባቸው የክልሉ አካባቢዎች ተከሰተ የተባለውን ይህን በሽታ እያጣራ ስለመሆኑም አስታውቋል
የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ነዳጅ በሚወጣባቸው የሱማሌ ክልል አካባቢዎች በተከሰተ አዲስ በሽታ ሰዎች ሞተዋል መባሉን አስተባበለ
በሱማሌ ክልል ምንነቱ ያልታወቀ አዲስ በሽታ ተከስቶ ሰዎች ለህመምና ለሞት እየተዳረጉ ነው መባሉን የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስተባብሏል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ አጠቃላይ ሁኔታውን ለማወቅ የሚያስችል ማጣራትን ከክልሉ ጤና ቢሮ ከአካባቢው ማህበረሰብ እና በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ የነዳጅ ተቋማት ጋር በመሆን እያደረገ እንደሆነም ነው ያስታወቀው፡፡
ሰዎች እየታመሙ እና እየሞቱ ነው በሚል የዘገቡት የውጭ ብዙሃን መገናኛዎች መረጃውን ከየት እንዳመጡት እንደማያውቅም ገልጿል፡፡
እስካሁን ባለን መረጃ መሰረት ምንም ዓይነት ያጋጠመ የህመም ሆነ የሞት አደጋ የለም ያሉት በኢንስቲትዩቱ የበሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ወሰን በሽታውን በተመለከተ ቀደም ሲል ያገኘነው መረጃ ቢጫ ወባ ነው የሚል ነበር ሲሉ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው ከተሰማሩ የነዳጅ ተቋማት በሚወጡና ህብረተሰቡ በሚገለገልባቸው የኬሚካል መያዣ ጄሪካዎች ምክንያት የመጣ እንደሆነ የሚያመለክቱ መረጃዎች ከክልሉ ጤና ቢሮ ተገኝተው እንደነበርም ነው የገለጹት፡፡
ሆኖም ማረጋገጫዎች አልተገኙም፡፡
ኢንስቲትዩቱ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ሲያጋጥሙ አስፈላጊውን ማጣራት አድርጎ ምን መደረግ እንዳለበት ምክረ ሃሳብ ያስቀምጣል ያሉት ተጠባባቂ ዳይሬክተሩ ከአሁን ቀደምም እንዲህ ዓይነት ችግር ዌስት ኢዊ በተባለ የክልሉ አካባቢ አጋጥሞ አስፈላጊው እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡
ዶቦ ዋይ በተባለው ወረዳ አጋጠመ ከተባለው ከዚህ የህብረተሰብ ጤና ችግር ጋር በተያያዘ የደረሰ ጉዳት ካለ ማጣራቱ ሲጠናቀቅ በቀጣዩ ሳምንት ለሚዲያ ይፋ እናደርጋለንም ብለዋል፡፡
ዘጋርዲያን የተሰኘው ተነባቢ የእንግሊዝ ጋዜጣ ከሰሞኑ በቻይና ኩባንያዎች በኩል ነዳጅ በሚወጣባቸው የሶማሌ ክልል ኦጋዴን አካባቢዎች በተለይም ካሉብ በተባለ ቦታ ከነዳጅ ተቋማቱ በሚወጣ መርዛማ ኬሚካል ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች እስከሞት ያደረሰ ጤና እክል እየገጠማቸው እንደሆነ መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡