ረቂቅ ስምምነቱ የሶስቱ ሀገራት የድርድርም ሆነ የሕግ እና ቴክኒክ ቡድኖች ውይይት ውጤት አይደለም
ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበትን ስብሰባ ተከትሎ የወጣውን የፕሬስ መግለጫ እንደማትቀበል አስታወቀች
ስብሰባው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ጠይቃ ሳለ ያልተሳተፈችበትን ስብሰባ ተከትሎ በአሜሪካ ግምጃ ቤት ዲፓርትመንት ሴክሬታሪ የወጣውን መግለጫ እንደማትቀበል ኢትዮጵያ አስታወቀች፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአሜሪካ የግምጃ ቤት ዲፓርትመንት ሴክሬታሪ በየካቲት 21 ቀን 2012 ዓ.ም (እ.ኤ.አ. በ28 ፌብሩዋሪ 2020) የፕሬስ መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ ዛሬ እኩለ ቀን አካባቢ ጀምሮ አስቸኳይ ስብሰባን ከሃገሪቱ ተደራዳሪ ቡድን አባላት ጋር አድርገዋል፡፡
መግለጫውን በከፍተኛ ቅሬታ መመልከታቸውንም ነው ከስብሰባው መልስ ባወጡት መግለጫ ያስታወቁት፡፡
”የግድቡ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በመርሆዎች መግለጫ ስምምነቱ መሰረት የግድቡን ሙሌት ከግንባታው ትይዩ በፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም እና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርሆዎች መሰረት የምታከናውን ይሆናል“ም ብለዋል፡፡
በመግለጫው ኢትዮጵያ የግድቡን የመጀመሪያ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ መመሪያ እና ደንብ ለማዘጋጀት የሚደረገው ድርድር ተጠናቋል በሚል የተሰጠውን መግለጫ እንደማትቀበል ያስታወቁ ሲሆን የግድቡ ሙሌት ከግንባታው ትይዩ በፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም እና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርሆዎች መሰረት እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡
”በዋሽንግተን ዲሲ የግብጽ ዐረባዊት ሪፐብሊክ ፈርሞበታል የተባለው “ረቂቅ” የሶስቱ ሀገራት የድርድርም ሆነ የሕግ እና ቴክኒክ ቡድኖች ውይይት ውጤት አይደለም። የቴክኒክ ጉዳዮች ድርድሩም ሆነ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቱ ላይ የሚደረገው ድርድር አልተጠናቀቀም፡፡ ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ መመሪያ እና ደንብ የሚዘጋጀው በሶስቱ ሀገራት ብቻ እንደሆነ አቋሟን ቀድማ አሳውቃለች“ ሲልም ነው መግለጫው የሚያስቀምጠው፡፡
ኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳን በሚያውቁት እና በተስማሙበት እንዲሁም በመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መርህ አንቀጽ ስምንት አድናቆታቸውን በሰጡት ሂደት መሰረት ሁሉንም የግድብ ደህንነት የሚመለከቱ ጉዳዮች በዓለምአቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ምክረ ሃሳብ መሰረት የተሰጡትን ምክረ-ሃሳቦች መፈጸሟን ትቀጥላለች ሲልም ያትታል፡፡
ኢትዮጵያ የግድቡን የመጀመሪያ ሙሌት፣የውሃ አለቃቅ መመሪያና ደንብን ለማዘጋጀት እና ቀሪ መሰረታዊ ልዩነቶችን ለመፍታት ከግብጽ እና ሱዳን ጋር የጀመረችውን ሂደት ለመቀጠል ቁርጠኛ ስለመሆኗም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡