“የኢትዮጵያን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከግምት ያላስገባ ጫና በሀገራዊ ሉዓላዊነታችን እና ጥቅማችን ላይ የሚሰነዘር ጥቃት” አድርገን እንወስደዋለን-ኢዜማ
በግድቡ ጉዳይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት እንዲቆም ኢዜማ ጥሪ አቀረበ
ግድቡን በተመለከተ በአሜሪካ የተሰጠው መግለጫ ሶስቱ ሃገራት እ.ኤ.አ በ2015 የፈረሙትን የመርህ ስምምነት ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንደሆነ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አስታወቀ፡፡
“ኢትዮጵያ የድርድሩ ቀን እንዲተላለፍ አስቀድማ ጥያቄ ያቀረበችበት እና ያልተሳተፈችበትን ውይይት ተከትሎ የግድቡ ሥራ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ሦስቱ ሀገራት ውጪ በሆነ ሀገር መንግሥት” የተሰጠው መግለጫው ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ሳትሳተፍባቸው የተፈጸሙ የቅኝ ግዛት ጊዜ ስምምነቶችን የሚያስታውስ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ያለው ፓርቲው “የኢትዮጵያን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከግምት ያላስገባ ጫና በሀገራዊ ሉዓላዊነታችን እና ጥቅማችን ላይ የሚሰነዘር ጥቃት” አድርገን እንወስደዋለን ብሏል፡፡
”ግድቡ ከጅማሬው አንስቶ ብዙ ውስብስብ ችግሮች የነበሩበት ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ዋጋ የከፈለበት እና እየከፈለበት የሚገኝም ሀገራዊ ምልክት ነው“ ያለም ሲሆን “ለኢትዮጵያ ከሚያስገኘው የኢኮኖሚ ጥቅም በዘለለ የአባይ ወንዝ ተፋሰስ ሀገራትን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና ሉዓላዊነትን ያዘለ ፕሮጀክት” እንደሆነም ገልጿል፡፡
በመሆኑም በግድቡ ዙሪያ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት እንዲቆምና በሀገር ጥቅምና ሉዓላዊነት ላይ አለመደራደሩን በቆራጥነት እንዲያሳይ ጠይቋል፤ ጉዳዩን በተመለከተ በሚደረጉ ሃገራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በቀዳሚነት እንደሚሰለፍ በመጠቆም፡፡
የተፋሰሱ ሀገራት፣ የአፍሪካ ሕብረት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ጎን እንዲቆሙ እና አቋማቸውንም በግልጽ እንዲያሳውቁ በጠየቀበት መግለጫው ፕሮጀክቱን ለመልካም ጉርብትና ማዋል እና “ለኢትዮጵያ እና ለሕዝቧ በጎ ለማይመኙ ኃይሎች መሣሪያ እንዳይሆን ነቅቶ መጠበቅ” እንደሚገባም አሳስቧል፡፡