በድርድሩ ሂደት ከሚመጣው ጫና ኢትዮጵያን ሊታደጋት የሚችለው ኃይል ማመንጨት መጀመር ነው-አህመድ ዘካሪያ (ፕ/ር)
ኢትዮጵያን ሊታደጋት የሚችለው ኃይል ማመንጨት መጀመር ብቻ ነው-ፕ/ር አህመድ ዘካሪያ
የአሜሪካን መግለጫ አስመልክቶ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር የስልክ ቆይታ ያደረጉት እውቁ የታሪክ ምሁር አህመድ ዘካሪያ (ፕ/ር) አሁን ያለው የድርድር ሂደት ከሚያመጣው ጫና ኢትዮጵያን የሚታደጋት ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ብቻ ነው ብለዋል፡፡
የግድቡ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት የተፋሰሱ ሃገራት የስምምነት ማዕቀፍ ተፈርሞ ቢጠናቀቅና ግንባታው በታሰበው ልክ ሄዶ ቢሆን ጥሩ እንደነበር ያነሱት ምሁሩ ኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ ሃገራቱን ከመለመን ውጭ ያንን ማድረግና የአሜሪካን አቋም ማስቀየር እንደማትችል ገልጸዋል፡፡
አሜሪካ በድርድሩ ሂደት መግባቷ በግብጽ እና እስራዔል መካከል እ.ኤ.አ በ1978 የተፈረመውን የካምፕ ዴቪድ ስምምነት ለማስጠበቅ በማሰብ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡
እንደ ምሁሩ አገላለጽ በስምምነቱ መሰረት እስራዔል የአባይን ውሃ የመጠቀም ፍላጎት አላት፡፡
“እናንተ ከተጠቀማችሁ በኋላ እንጠቀማለን” የሚል ሃሳብን የያዘ የስምምነቱ አንቀጽ መኖሩ ለዚሁ ማሳያ ነውም ብለዋል፡፡
አሜሪካ ለመካከለኛው ምስራቅ ሰላምና መረጋጋት ይበጃል በሚል በቅርቡ አዲስ የሰላም እቅድ ይፋ ማድረጓም የሚታወስ ነው፡፡
ግብጾቹ “አሁንም የመቆጣጠርና የግድቡ ጌታ የመሆን ስሜት እንዳደረባቸው ናቸው” ያሉት የታሪክ ተመራማሪው ኢትዮጵያ እጅ ላለመስጠት ግድቡ ኃይል እንዲያመነጭ ማድረግ እንደሚጠበቅባት ተናግረዋል፡፡