መንግስት በ“ህግ ማስከበር ዘመቻ”ወቅት በንጹሃን ላይ በደረሰው ጉዳት ማዘኑን ገለጸ
የፌደራል መንግስትና ሕወኃት ወደ ግጭት የገቡት ባለፈው ጥቅምት ወር ነበር
መንግስት በተለያዩ የአለምአቀፍ ሚዲያዎች የሚወጡት የንጹሃን ጉዳት ሪፖርቶች በመረጃ ያልተደገፉና የፖለቲካ አላማ ያላቸው ናቸው ብሏል
የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል በተካሄደረው “የህግ ማስከበር ዘመቻ” ወቅት በንጹሃን ላይ በደረሰው ማንኛውም ጉዳት ማዘኑን ገልጿል፡፡ መንግስት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሪጃ ማጣሪያ ፌስቡክ ገጽ እንዳስታወቀው “የአንድ ንጹሃን ሰው ሞት ብዙ” ነው ብሏል፡፡
መንግስት ብዙ የሚባል የንጹሃን ሞት አለማጋጠሙንና ይህም የዘመቻውን በጥንቃቄ መታቀድና የመከላከያ ሰራዊትን ሙያ የተለባሰ እንቅስቃሴ እንደሚያሳይ አስታውቋል፡፡
መንግስት በተለያዩ የአለምአቀፍ ሚዲያዎች የሚወጡት የንጹሃን ጉዳት ሪፖርቶች በመረጃ ያልተደገፉና የፖለቲካ አላማ ያላቸው ናቸው ሲል አጣጥሎታል፡፡
የፌደራል መንግስት “የህግ ማስከበር ዘመቻ” የጀመረው ባለፈው ጥቅምት ወር የትግራይ ክልልን የሚመራው ሕወሓት በመከላከያ ሰራዊ ላይ ጥቃት ሰንዝሯል ማለቱን ተከትሎ ነው፡፡
ፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ወደ ጦርነት ካመራ በኋላ በትግራይ ክልል የጸጥታ መደፍረስ አጋጥሞ ቆይቷል፡፡በሁለቱ መካከል የነበረው አለመግባባት ወደ ግጭት ያመራው የትግራይ ክልልን ይመራ የነበረው ህወሓት ከምርጫ ቦርድ ተቃራኒ በመቆም የራሱን ክልላዊ ምርጫ ቦርድ በማቋቋሙና ምርጫ በማካሄዱ ነበር፡፡
የፌደራል መንግስት “የህግ ማስከበር” ባለው ዘመቻ የህወሓት አባላትንና ተባባሪ ነበሩ ያላቸውን ወታደራዊ ቡድኖች በማደን ላይ ሲሆን እስካሁን ከቀድሞ የህወሃት አመራሮች መካከል የተያዙ፤የተገደሉና፤እየተፈለጉ ያሉም አሉ፡፡
በትግራይ ክልል በግጭቱ ሳቢያ በሚሊዮን የሚቆሩ ሰዎች ለረብ መዳረጋቸውን በእነ ዶ/ር ሙሉ ነጋ የሚመራው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አስታውቋል፡፡ በክልሉ ሰብአዊ ቀውስ መከሰቱን የተለያዩ የመብት ድርጅቶችም በተለያየ ጊዜ ገልጸዋል፡፡
የፌደራል መንግስት ግጭት ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች ለሰብአዊ እርዳታ የሚውል ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶችን እየላከ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡
ምርጫ ቦርድ ህወሃት በህገወጥ እንቅስቃሴ መሳተፉ በመረጋገጡ ከህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ ዝርዝር ውስጥ መሰረዙንና በፓርቲው ስም የሚንቀሳቀሱ ሰዎች እውቅና እንደማይኖራቸው ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ በትናንትናው እለት 49 የፖለቲካ ፓርቲዎች ግንቦት 28 ለሚካሄደው ምርጫ የሚወዳደሩበትን ምልክት ምርጫ ቦርድ ይፋ አድርጓል፡፡