በትግራይ ክልል በተፈጸሙ ወንጀሎች በሕግ ከሚፈለጉ 349 ሰዎች 124ቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ
ሕወሓት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚፈጠሩ ሁከቶች ገንዘብ የሚከፍለው “ውጤታማነታቸውን መርምሮ ሲታመንባቸው ነበር” ተብሏል
በማይካድራው ግድያ ከሚፈለጉ 279 ተጠርጣሪዎች 36ቱ ሲያዙ አብዛኛው ወደ ሱዳን አምልጠዋል ተባለ
በትግግራይ ክልል ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ እና በሌሎች አካባቢዎች ስለተፈጸሙ ወንጀሎች እና ስለተከናወኑ የወንጀል ምርመራ ተግባራት ዛሬ ጥር 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
በክልሉ በተፈጸሙ ወንጀሎች የተጠረጠሩ እና የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸው ሰዎች ብዛት 349 መሆናቸውን የገለጹት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር ጄኔራል እና የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ዘላለም መንግስቴ ፣ ከነዚህ ውስጥ 96 የሚሆኑት የሕወሓት ቁልፍ አመራሮች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ተፈላጊ ከሆኑት አጠቃላይ ተጠርጣሪዎች 124 የሚሆኑት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ሲሆን ሌሎቹን በቁጥጥር ስር አውሎ በህግ ለመጠየቅ ከመከላከያ እና በአካባቢው ካሉ የጸጥታ ኃይሎች ጋር በጥምረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የወንጀል ምርመራ ስራው ሰፊ በመሆኑ ጥልቅ የሆነ ምርመራ መከናወኑን የገለጹት ም/ል ኮሚሽነር ጄኔራሉ ፣ ተጠርጣሪዎቹ በወንጀል መሳተፋቸውን የሚያመላክቱ እና የሚያረጋግጡ ከ 680 በላይ የሰው እና የሰነድ ማስረጃ የማሰባሰብ ስራም መሰራቱን አስረድተዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ፍቃዱ ጸጋ በበኩላቸው “የወንጀል ቡድኑ” ዋናውን ወንጀል ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ቢፈጽምም “ለ27 ዓመታት ይዞት ከነበረው ስልጣን ለቆ ወደ ትግራይ ክልል ከተመለሰበት ጊዜ ጀምሮ በከፍተኛ የዝግጅት ሂደት ውስጥ የቆየ መሆኑን” ገልጸዋል፡፡ ከፌዴራሉ መከላከያ ሰራዊት አወቃቀር ጋር የሚመሳሰል አደረጃጀትን በመዘርጋት ለውጊያ ብቁ የሆኑ የልዩ ሀይል አባላትን ሲመለምል እና ሲያሰለጥን መቆየቱንም አረጋግጠዋል፡፡ በ2011 እና በ2012 ዓ.ም ብቻ ከ84,000 በላይ የሚሆኑ የልዩ ኃይል አባላትን መልምሎ ለውጊያ አዘጋጅቶ እንደነበር አክለው የገለጹት አቶ ፈቃዱ ፣ አባላቱን በ8 እዞች 23 ሬጅመንቶችን በቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባል የነበሩ ጡረተኞችን በማካተት የዝግጅት ስራ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
“የወንጀል ቡድኑ” በትግራይ ክልል ከፈጸማቸው ወንጀሎች ባሻገር ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች ምክንያት የሚሆኑ ረብሻዎችን በገንዘብ ሲደግፍ የነበረ ሲሆን የገንዘብ አደጋገፉም በዘፈቀደ የሚደረግ ሳይሆን “የሁከት ፈጠራው ውጤታማነት ተመርምሮ እና ሁከቱን ለማድረግ ያቀደው እና የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄ ያቀረበው ግለሰብ ወይም ቡድን በአካል ቀርቦ አብራርቶ ሲታመንበት የሚፈቀድ ነበር” ነው ያሉት፡፡
ከማይካድራው ዘግናኝ ጥቃት ጋርም በተያያዘ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ሲገልጹ ፣ ብሔርን መሰረት ባደረገ መልኩ በተፈጸመው የሰዎች ግድያ የተሳተፉ 279 ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን ከተሰበሰቡ ማስረጃዎች መረዳት የተቻለ ሲሆን አብዛኛው ተጠርጣሪዎች ወደ ሱዳን ሲያመልጡ 36 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራቸው ተጠናቆ የክስ ዝግጅት የሚቀረው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ጥቃት ጋር በተያያዘ የሟቾች ቁጥር ከጤና ሚኒስቴር የተላከው የሀኪሞች ቡድን ከ117 ጉድጓዶች የተገኙ አስክሬኖችን መርምሮ የሟቾቹን ብዛት እና የሞት ምክንያት እስኪያሳውቀን ድረስ ትክክለኛው በጥቃቱ የሞቱ ሰዎችን ብዛት መግለጽ ለጊዜው አልተቻለም ነው ያሉት፡፡ መሬት ባለው እውነት እና በየሚዲያው በተገለጸው መካከል ልዩነት እንዳለ አቶ ፈቃዱ በማብራሪያቸው አስረድተዋል፡፡ መረጃዎቹን በሰጡ የሚዲያ ተቋማት ዘጋቢዎች ጋር በተደረገ የማጣራት ስራ በወቅቱ አስክሬኖች ይሸቱ ስለነበር ተጠግቶ ለመቁጠር የማይቻል በመሆኑ ቁጥሩን የገለጽነው በግምት ነበር ብለው እንደተናገሩም አክለው ተናግረዋል፡፡
አቶ ፍቃዱ የምርመራውን ስፋት እና ሁኔታ ሲያብራሩም የወንጀል ምርመራው ከጥቅምት 24/ 2013 ዓ.ም በኋላ የተፈጸሙትን ወንጀሎች ብቻ ሳይሆን ተጠርጣሪዎቹ በስልጣን ላይ በነበሩባቸው 27 ዓመታት የፈጸሟቸውም ወንጀሎች እንደሚያካትት ገልጸዋል፡፡ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መረጃ እንደሚያሳየው ምርመራው ሲጠናቀቅ በህይወት በተገኙት ላይ የሕግ ተጠያቂነትን ለማስፈን እንዲሁም በሞቱት ላይ ደግሞ ምርመራው ቀጥሎ ነገር ግን ለጥናት እና ምርምር ስራዎች ወይም ለዕርቀ ሰላም ጉዳዮች ስራ እንዲውል ታሪክን ለማኖር ጥረት ይደረጋለ ብለዋል፡፡