በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፤ መንግስት በሽብር የጠረጠረውን ማንኛውንም ሰው በቁጥጥር ስር እንደሚያደርግ አስታወቀ
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በ48 ሰአታት ውስጥ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ይቀርባል
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽመው “የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ዕዝ” ነው ተብሏል
የኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው የአስቸኳይ ስብሰባ በመላ ሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን የፍትሕ ሚኒስትሩ አስታወቁ፡፡
የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዴዎን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በዚህ ጉዳይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡አዋጁ የታወጀው በሀገር የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ በመደቀኑና፤ ይህንንም አደጋ በመደበኛ ሁኔታ መቆጣጠር ባለመቻሉ የጸጥታና የደህንነት ተቋማትንና ዜጎችን በማቀናጀት አደጋውን ለመቀልበስ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር ለማድረግ ነው ብለዋል ጌዴዎን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ፡፡
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በ48 ሰዓታት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ የተገለጸ ሲሆን ተፈጻሚ የሚሆነው ግን ከዛሬ ጀምሮ ነው፡፡
ይህንን አዋጅ የሚያስፈጽመው “የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ዕዝ” ሲሆን ይህም የሚመራው በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ስር እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ ይህ ዕዝም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ (ለጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ) እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
ዕዙ የሀገሪቱን ሁሉንም የጸጥታ አካላት ማዘዝና ማንቀሳቀስ እንደሚችል ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም የተቋቋመው ዕዝ ማንኛውንም መሳሪያ የታጠቀ አካልን የማዘዝና የማሰማራት ስልጣን እንደተሰጠው ጌዲዎን ጢሞቲዮስ ተናግረዋል፡፡
የታጠቁ ኃይሎች ወደ ግዳጅ እንዲሰማሩ፤ መሰማራት የማይችሉ ከሆነ ደግሞ የታጠቁትን በአዋጁ መሰረት የመገናኛ ዘዴዎችንና የትራንስፖርት አገልግሎትን የመዝጋት ስልጣን የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ዕዝ እንደሚሆንም ነው የተገለጸው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በሽብር ከፈረጀው ቡድን ጋር ግንኙነት አለው ብሎ የጠረጠረውን ማንኛውንም ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝና ተጠያቂ ማድረግ እንደሚቻልም ነው የተገለጸው፡፡ የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ዕዝ፤ መንግስት በሽብር ከፈረጀው ቡድን ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ የጠረጠረውን ድርጅት ወይም ግለሰብ ቤትና ንብረት ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መበርበር እንደሚችልም አዋጁ ስልጣን ሰጥቶታል፡፡
ሚኒስቴሩ፤የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፎ የተገኘ ሰው፤ ቀላለ ወንጀል ከሆነ እስከ ሶስት አመት የሚያስቀጣ ሲሆን ከባድ ወንጀል ከሆነ ደግሞ እስከ 10 አመት የሚፈጅ እስራት እንደሚያስቀጣ አስታውቋል፡፡