በሱዳን የተቃውሞ ሰልፍ 3 ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጁ
በሱዳን ያለው ሁኔታ በሽግግር ላይ ለምትገኘው ሀገር እና ለሽግግሩ መንግስት ከፍተኛ ፈተና ሆኗል
ከዳቦ ጥያቄ ጋር በተያያዘ በሱዳን የተጀመረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ባለፉት 3 ቀናት ተባብሷል
በሱዳን ካለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በደቡብ እና በሰሜን ዳርፉር እንዲሁም በሰሜን ኮርዶፋን ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን የሱዳን ዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
ባለፉት ሶስት ቀናት በተካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ እና የኃይል እና የዝርፊያ ድርጊቶች ምክንያት ሶስት የሱዳን ግዛቶች ማክሰኞ ዕለት የአስቸኳይ ጊዜ ማወጃቸውን ነው ዘገባው ያመለከተው፡፡
በደቡብ ዳርፉር ግዛት የተቋቋመው የፀጥታ ኮሚቴ በግዛቱ ዋና ከተማ ኒያላ ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ ማለዳው 12 ሰዓት መንቀሳቀስ እንደማይቻል አስታውቋል፡፡ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም እንዲዘጉ መወሰኑም ከእርምጃዎቹ መካከል ናቸው፡፡
የተቃውሞ ሰልፈኞች በኒያላ ሱቆችን መዝረፍ ሲጀምሩ ፖሊሶች ሰልፈኞቹን መበተናቸውንገ የግዛቱ ገዥ ሙሳ ማህዲ ገልጸዋል፡፡
የጦር መሳሪያ ጭምር ይዘው የወጡ ሰልፈኞች መኖራቸውን የገለጹት የግዛቱ ገዥ ሙሳ ፣ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ሰልፈኞች ስለመኖራቸውም ተናግረዋል፡፡
ሌላው ከፍተኛ ተቃውሞ የነበረበት የሰሜን ዳርፉር ግዛት የፀጥታ ኮሚቴም እንዲሁ ማክሰኞ ዕለት በመላ ክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡ ከምሽት 12 ሰዓት እስከ ማለዳ 12 ሰዓት የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለበት በዚሁ ግዛት ፣ ትምህርት ቤቶች ፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና የገበያ ስፍራዎች እንዲዘጉም ተወስኗል፡፡ ጎዳናዎችም ለአገልግሎት ዝግ እንዲሆኑ የተወሰነ ሲሆን በቡድን ሆኖ ወይም ተሰባስቦ መገኘትም በጥብቅ ተከልክሏል፡፡
በሰሜን ኮርዶፋን ግዛትም እንዲሁ ተመሳሳይ እገዳዎች መጣላቸው ተዘግቧል፡፡ የሰሜን ኮርዶፋን አስተዳዳሪ የሆኑት ካሊድ ሙስጠፋ አደም የዋና ከተማው የአል-አብያድ ገበያዎች እና የሌሎች ሁለት አከባቢዎች የገበያ ስፍራዎችም ለ 48 ሰዓታት (ለ 2 ቀናት) እንዲዘጉ ውሳኔ መተላለፉን አስታውቀዋል፡፡ ይህም ንብረቶችን ከዘረፋ እና ከጥቃት ለመጠበቅ በሚል የተወሰነ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡ በመላ ግዛቱ ከምሽት 12 እስከ ማለዳው 12 ሰዓት የሰዓት እላፊም ታውጇል፡፡
በምስራቅ ሱዳን እና በሌሎችም አንዳንድ አካባቢዎች አሁንም ህዝባዊ ተቃውሞው መቀጠሉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከሰልፎቹ ጋር ተያይዞ በሰው ላይ ስለደረሰው ጉዳት በዘገባው የተባለ ነገር የለም፡፡
ከዳቦ ፣ ከዱቄት ፣ ከነዳጅ እና ከምግብ ማብሰያ ጋዝ ጥያቄ ጋር ተያይዞ በሱዳን የነበረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ባለፉት ጥቂት ቀናት ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ በተቃውሞ ሰልፈኞቹ የተለያዩ ዘረፋዎች የተፈተሙ ሲሆን የፀጥታ ኃይል ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ንብረቶችም በእሳት ወድመዋል፡፡
በሱዳን ያለው ሁኔታ በሽግግር ላይ ለምትገኘው ሀገር እና ለሽግግሩ መንግስት ከፍተኛ ፈተና ሆኗል፡፡ ፕሬዝዳንት ኡመር አል በሽር ከስልጣን ተወግደው ከተመሰረተው ሽግግር በኋላ ከዶላር አንጻር የሱዳን ፓውንድ ዋጋ በከፍተኛ መጠን የወደቀ ሲሆን በሀገሪቱ የዋጋ ግሽበት እና አጠቃላይ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ተከስቷል፡፡