የሉአላዊ ምክር ቤት እና ሚኒስትሮች ምክር ቤት የፈረሰ መሆኑን አስታውቀዋል
በሱዳን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን የሱዳን ጦር አዛዥ ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን ገለጹ።
በሱዳን በሲቪል አስተዳድሩ ላይ መፈንቅለ መንግስት መካሄዱ ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎ የሱዳን ጦር አዛዥ ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን መግለጫ የሰጡ ሲሆን፤ በሀገሪቱ የአስቸኳ ጊዜ አዋጄ መታወጁን አስታውቀዋል።
ይሁንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ ጀነራል አልቡርሀን አልተናገሩም።
በዚህም መሰረት የሉአላዊ ምክር ቤት እና ሚኒስትሮች ምክር ቤት የፈረሰ ሲሆን፤ የክልሎች አሰተዳዳሪዎች እና ሌሎች አመራሮች ከስልጣን ተነስተዋል ብለዋል።
በሱዳን በሲቪል አስተዳድሩ ላይ መፈንቅለ መንግስት የተካሄደ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክን ጨምሮ በርካታ የሲቪል አስተዳድሩ አመራሮች በእስር ላይ ናቸው።
ሌሊት ከተጀመረው መፈንቅለ መንግስት በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን የካቢኔ ጉዳዮች ፤ የኢንዱስትሪ እና የኢንፎርሜሽን ሚኒስትሮች መታሰራቸው ተረጋግጧል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚዲያ አማካሪ ፋይሳል መሐመድ ሳሌህ ቤተሰቦች ቤትም በጸጥታ ኃይሎች ከበባ የተደረገበት ሲሆን የአረብ ሶሻሊስት ባአስ ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አሊ ለ ሪህ አል ሳን ሃውሪም ታስረዋል።
ከሰሞኑ ለተቃውሞ በአደባባይ የሰነበቱት ሱዳናውያን አሁንም ወደ ካርቱም አደባባይ በመውጣት ተቃውሞ ማሰማት ጀምረዋል።
አሁን ላይ የካርቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላና ማረፊያ የተዘጋ ሲሆን፤ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎትም ተቋርጧል ነው የተባለው፡፡
ሱዳን በቅርቡ ወታደራዊ አመራሩ አከሸፍኩት ያለው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አጋጥሟት እንደነበር ይታወሳል።