መንግስት በአዲስ አበባ “የሽብር ጥቃት” ሊያደርሱ የነበሩ 454 ተጠርጣሪ ግለሰቦችን መያዙን አስታወቀ
ግብረኃይሉ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በጋምቤላ ክልሎች ያሉ ወቅታዊ ያሉ የጸጥታ ሁኔታዎችን ዳሷል
ሽብር ሊፈጽሙ ነበር የተባሉት ተጠርጣሪዎች በመያዛቸው ሊያደርሱት የነበረው ጥቃት ከሽፏል ብሏል ግብረ ኃይሉ
የፌደራል መንግስት የጋራ የጸጥታ እና የደህንነት ግብረ ኃይል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ወደ አዲስ ከተማ ዘልቀው በመግባት የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ነበር ያላቸውን ግለሰቦች መያዙን አስታውቋል፡፡
ግብር ኃይሉ እንዳስታወቀው በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ በተደረገ ኦፕሬሽን 454 ተጠርጣሪዎችን መያዙን ገልጿል፡፡
“የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 174 የህወሓት ጁንታ ቡድን አባላት፣ 98 የሸኔ ቡድን አባላት፣ 51 ጽንፈኛ የፋኖ አባላት፣ በከተማው ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩ 100 ተጠርጣሪዎች እና 31 የአልሸባብና የአይ.ኤስ.ኤስ አባላትን በድምሩ 454 ተጠርጣሪዎች ” ግብረ ኃይሉ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ሽብር ሊፈጽሙ ነበር የተባሉት ተጠርጣሪዎች በመያዛቸው ሊያደርሱት የነበረው ጥቃት ከሽፏል ብሏል ግብረ ኃይሉ፡፡
ግብረኃይሉ በመግለጫው ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በጋምቤላ ክልሎች ያሉ ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታዎችን ዳሷል፡፡
በጋምቤላ ክልል “የህወሃት ጁንታ ቡድን አባላት፣ የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ)፣ የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅንቄ (ጉህዴን) እና የኦነግ-ሸኔ አሸባሪዎች ተደራጅተውና ተቀናጅተው በጋምቤላ ክልል በጋምቤላ ከተማና በአካባቢው” ጥቃት ማድረሳቸውን የገለጸው ግብረ ኃይሉ 137 ሽብር ቡድን አባላት ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡
በጋምቤላ የነበረው የጸጥታ ችግር ተወግዶ ጋምቤላ ክልል አሁን ሰላም ነው ብሏል ግብረ ኃይሉ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ ጊምቢ ከተማ አካባቢ በሚገኘው የቶሌ ቀበሌ በንጹሃን ላይ የደረሰውን ዘግናኝ ግድያ ያስታወሰው የግብረ ኃይሉ መግለጫ የመንግስት የጸጥታ ኃይል በሽብር ቡድኑ አባላት ላይ ርምጃ ወስዷል ብሏል፡፡
ግብረኃይሉ “በጽንፈኛ የፋኖ አባላት” ላይ እርምጃ መወሰዱን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት የአማራ ክልል የነበረው የጸጥታ ችግር ተወግዶ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ መደረጉን አስታውቋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ወቅት ከ”ጁንታው” ጋር ተፋልዋል ያላቸውን የፋኖ አባላት ያወደሰ ሲሆን በክልሉ በአፍራሽ እንቅስቃሴ ተሳትፈዋል ያላቸው 5ሺ 804 ተጠርጣሪዎችን መያዙን ገልጿል፡፡
aXA6IDMuMTQ3LjQyLjE2OCA= ejasoft island