"ሸኔ እና "የጋምቤላ ነጻ አውጭ ግንባር" ትናንት ተኩስ መክፈታቸው ተገልጾ ነበር
በጋምቤላ ከተማ ዛሬም ተኩስ እንዳለ ነዋሪዎች ለአል ዐይን አማርኛ አረጋግጠዋል።
"ሸኔ እና "የጋምቤላ ነጻ አውጭ ግንባር" ትናንት ተኩስ መክፈታቸው ተገልጾ ነበር።
ርዕሰ መስተዳድር ኡመድ ኡጁሉ በጋምቤላ ከተማ በነበረው ተኩስ በከተማው በሚገኙ የመንግስት ተቋማት ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱን ትናንትና ገልጸዋል።
አል ዐይን አማርኛ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ ስራ አለመሄዳቸውንና ተኩስ እየሰሙ መሆኑን ገልጸዋል።
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ተኩስ በከፈቱት ላይ እርምጃ እየወሰዱ እንደሆነ ያነሱት ነዋሪዎቹ ተኩሱ አልፎ አልፎ እየተሰማቸው እንደሆነ አንስተዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ዑመድ ትናንት ተኩስ የከፈቱት ቡድኖች የርዕሰ መስተዳድሩን ጽ/ቤት እንደተቆጣጠረ ተደርጎ የተናፈሰው ወሬ ሀሰት መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።
በጋምቤላ ከተማ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር በክልሉ የሚገኙ የፀጥታ ሀይሎች ባካሄዱት ቅንጅታዊ ማጥቃት ከተማውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር መቻሉንም ገልጸዋል።
ተከፍቶ በነበረው ተኩስ ከሁሉም ወገን ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በከተማው ተኩስ ከፍተው በነበሩ ሃይሎች ላይ የፀጥታ አካላት በወሰዱት እርምጃ ከተማውን ማረጋጋት ተችሏል ብለዋል።