መንግስት አጋር ድርጅቶች ለአማራና አፋር ክልሎች የሚያደርጉትን ድጋፍ መጠን ከፍ እንዲያደርጉ ጠየቀ
በጥቃቱ ከ500ሺ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ተገልጿል
አለምአቀፉ ማህበረሰብ ለይቶ ማውገዙን ማቆም አለበት፤ የህወሃት ኃይሎች በሁለቱ ክልሎች ያደረሱትን ጥቃት ማውገዝ አለበት ብለዋል
የህወሃት ሃይሎች በአማራና በአፋር ክልል ባካሄዱት ጥቃት ለተፈናቀሉ ሰዎች የሚደረገው ሰብአዊ ድጋፋ በቂ አለመሆኑንና አጋሮች የሚያደርጉትን ድጋፍ መጠን ከፍ እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስቴር ጸ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ ከሁለቱ ክልሎች የተፈናቀሉት ዜጎች ቁጥር አሁን ላይ ከ500ሺ በላይ ማለፉንና ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
አለምአቀፉ ማህበረሰብ ለይቶ ማውገዙን ማቆም አለበት ያሉት ቢልለኔ ስዩም የህወሃት ኃይሎች በሁለቱ ክልሎች ባደረሱት ጥቃት የደረሰውን ገዳት ዘርዝረዋል፡፡ በጥቃቱ በአማራና በአፋር ንጹሃን ሆስፒታሎች፣ ባንኮችና ሌሎች የህዝብ መገልገያ መሰረተ ልማቶች ወድመዋል ብለዋል፤ ወድሟል ያሉትን በፎቶ አሳይተዋል፡፡
ቢልለኔ በመግለጫቸው በጥቃቱ ምክንያት በአጠቃላይ የ4.5 ሚሊዮን ሰዎች በተለያየ መልኩ መጎዳታቸውን አስታውቀዋል፡፡
የብሄራዊ አደጋ ማስተባበሪያ ማእከል፤ የአማራና አፋር ክልሎች የአደጋ እርዳታ ማስተባበሪያዎች ወደ ስራ መሰማራታቸውንና እርዳታ ለሚፈልጉ ሰዎች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ቢልለኔ ገልጸዋል፡፡
በትግራይ ክልልም አልፎአልፎ የእርዳታ መኪኖች በህወሃት ምክንያት እክል ቢገጥማቸውም ፤እርዳታው እየደረሰ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በአሻባሪነት የፈረጀው ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ቦታዎችን መቆጣጠሩንና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት አለማድረሱን መግለጹ ይታወሳል፡፡
በጥቅምት ወር 2013 የህወሓት ሃይሎች በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ባወጀው “ህግ ማስከበር ዘመቻ” ተጀመረው ግጭት አሁን ላይ 11 ወራት ሊሆነው ነው፡፡
የፌደራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፣ ሰራዊቱን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱን ተከትሎ የህወሓት ሃይሎች የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌን ጨምረው በርከታ ቦታዎች መቆጣጠር ችለዋል፡፡ትግራይን የተቆጣጠሩት የትግራይ ሃይሎች፤ ወደ አጎራባችና አማራና አፋር ክልል ጥቃት ከፍተው ቦታዎች ተቆጣጥረዋል፡፡
የህወሓት ኃይሎች ወደ አጎራባቸው ክልሎች ጥቃት መክታቸውን ተከትሎ የአማራ ክልል መንግስትና የፌደራል መንግስት የህወሓት ሃይሎችን ለመዋጋት የዘመቻ ጥሪ አቅርበዋል፤ጦርነትም እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የተናጠል ተኩስ አቁሞ የተፈለገውን ለውጥ አላመጣም ያለው የፌደራል መንግስት መከላከያ ሰራዊትና የክልል ልዩ ሃይሎች ጠንካራ እርምጃ እንዲወስዱ አቅጣጫ ማስቀመጡን መግለጹ ይታወሳል፡፡