ኢሰመኮ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ጉዳቶችን የሚመረምር የባለሞያዎች ቡድን ሊያሰማራ ነው
በመስፋፋት እና በመባባስ ላይ የሚገኘው ግጭት ሲቪል ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳትን እና ሰብዓዊ ቀውስን በማስከተል ላይ እንደሚገኝም ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው
ኮሚሽኑ በደብረታቦር ከተማ በህወሓት ታጣቂዎች እንደተፈጸመ በተነገረ የከባድ መሳሪያ ድብደባ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ 5 ሰዎች መገደላቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል የባለሞያ ቡድን ሊያሰማራ ነው በግጭቱ የተጎዱ አካባቢዎች ያለውን ሁኔታ ይመረምራል፡፡
በአሳሳቢ ሁኔታ በመስፋፋት ላይ ከሚገኘው የትግራይ ግጭት ጋር በተገናኘ የተፈጸሙ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ማድረስ፣ ግድያ፣ ዘረፋ እና መፈናቀል በተመለከተ ምርመራ ለማካሄድ ወደ አማራ ክልል አካባቢዎች የባለሞያ ቡድን ይልካል
ኮሚሽኑ መሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ/ም ከሰዓት በኋላ በክልሉ ደቡብ ጎንደር ዞን ደብረታቦር ከተማ ላይ በህወሓት ታጣቂዎች እንደተፈጸመ በተነገረ የከባድ መሳሪያ ድብደባ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑት ውዴ ዋሌ (ዕድሜ 50)፣ እሱባለው ድረስ (ዕድሜ 23)፣ አዲሳለም ድረስ (ዕድሜ 18)፣ሰርካለም ድረስ (ዕድሜ 26)፣ ህጻን አመል ድረስ (ዕድሜ 4 ወር) መገደላቸውን አረጋግጧል፡፡
በተጨማሪም በሟቾች ግቢ ተከራይተው ይኖሩ የነበሩ ሁለት ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ በመስፋፋት እና በመባባስ ላይ የሚገኘው ግጭት ሲቪል ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳትን እና ሰብዓዊ ቀውስን በማስከተል ላይ ነው፡፡
ኮሚሽኑ በግጭቱ የሚሳተፉ ሁሉም ወገኖች ሲቪል ሰዎችን በድጋሚ ዒላማ እንዳያደርጉ በድጋሚ አሳስቧል፡፡