ህወሓት ይህን ያለው ጠ/ሚ ዐቢይ ለትግራይ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ መሾማቸውን ተከትሎ ነው
ህወሓት የትግራይ ክልልን “በምስለኔ” ማስተዳደር አይቻልም አለ
ህወሓት ዛሬ ባወጣው መግለጫ የትግራይን ክልል “በምስሌነ ለማስተዳደር ማሰብ የቀን ቅዥት ነው” ብሏል፡፡
ህወሓት ይሄን ያለው ፣ የሚኒስትሮች ም/ቤት ዶክተር ሙሉ ነጋን በትግራይ ክልል ለተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ አድርጎ መሾሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዛሬው እለት ማሳወቃቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት የፌደሬሽን ምክርቤት የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ጣልቃ እንዲገባና ጊዜያዊ አስተዳዳር እንዲቋቁም ዉሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡
መግለጫው የትግራይ ህዝብ ህመንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ መሪዎች የሚመርጥ ስለሆነ “…በትግራይ ክልል ጊዚያዊ መንግስት” መዋቀሩን ክልሉ አይቀበልም ብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጥቅምት 24 ምሽት ህወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ማድረሱን ከገለጹ በኃላ በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የነበረው የቆየ አለመግባባት ተባብሶ ወደ ጦርነት አምርቷል፡፡
ግጭቱ ከተጀመረ በኋላ የትግራይን ክልል የሚመራው ህወሓት ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲኖር ፍላጎቱን ቢገልጽም የፌደራል መንግስት “የህገወጡ የህወሓት” ቡድን ህግ ፊት ሳይቀርቡ ድርድር እንደማይኖር ገልጿል፡፡
የተወካዮች ምክርቤት በትናንትናው እለት የክልሉን መሪ ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ብረሚካኤልን ጨምሮ የ39 የምክርቤት አባላትን ያለመከሰሰ መብት አንስቷል፡፡ በትናንትናው ምሽት ጠቅላይ አቃቤ ህግ በህወሓት መሪዎች ላይ የፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዝ አውጥቶባቸዋል፡፡
በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል ያለው አለመግባባት የጀመረው ኢትዮጵያን ለ27 አመታት ሲመራ የነበረው ኢህአዴግ ፈርሶ ብልጽግና ፓርቲ ሲመሰረት፣ ከመስራቾቹ አንዱ የነበረው ህወሓት የውህደቱ አካል አልሆንም ባለበት ወቅት ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ የፌደራል እና የክልል የጸጥታ ሃይሎች የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት እንዲጠብቁና ሰብአዊ መብትን እንዳይጥሱ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡