የትግራይ ልዩ ሃይል በሚቀጥሉት 2 እና 3 ቀናት ለሰራዊቱ እጅ እንዲሰጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቀረቡ
“የትግራይ ህዝብ ቡድኑ የቀናት ዕድሜውን ለማራዘም ሲል የሚያስተላልፈውን ጥሪ ባለመቀበል ልጆቹን ከከንቱ መስዋዕትነት እንዲጠብቅ”ም አሳስበዋል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ወንጀለኛ”ያሉት የህወሓት ቡድን “በሁሉም አቅጣጫ ተከቦ” እንደሚገኝ አስታውቀዋል
የትግራይ ልዩ ሃይል በሚቀጥሉት 2 እና 3 ቀናት ለሰራዊቱ እጅ እንዲሰጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቀረቡ
የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል እያካሄደው ያለውን ህግ የማስከበርና የሃገር ህልውና እርምጃ አስመልክተው ለትግራይ ህዝብ በትግርኛ ቋንቋ መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የትግራይ ልዩ ሃይል እና ሚሊሻ በሚቀጥሉት 2 እና 3 ቀናት እጁን ለሰራዊቱ እንዲሰጥ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የልዩ ኃይል እና የሚሊሻ አባላቱ “ስግብግቡ ጁንታ የህወሓት ቡድን የቀናት ዕድሜውን ለማራዘም ሲል የሚያስተላልፈውን ጥሪ ባለመቀበል ከከንቱ መስዋዕትን ራሳቸውን እንዲቆጥቡ”ም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“ወንጀለኛ”ያሉት ቡድኑ እየተወሰደበት ባለው እርምጃ “በሁሉም አቅጣጫ ተከቦ” እንደሚገኝም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
እየደረሰበት ባለው በዚህ ከፍተኛ ኪሳራ “ጦር ግንባሮች ላይ ተገኝቶ አመራር ለመስጠት ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል”ም ብለዋል፡፡
በመሆኑም “የትግራይ ህዝብ ቡድኑ የቀናት ዕድሜውን ለማራዘም ሲል የሚያስተላልፈውን ጥሪ ባለመቀበል ልጆቹን ከከንቱ መስዋዕትነት እንዲጠብቅ” አሳስበዋል፡፡
በክልሉ የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የሚሰሩ አመራሮች “እየተወሰደ ያለው እርምጃ ህግ የማስከበር መሆኑን ተረድተው ለሃገር ህልውና ሲሉ ከመከላካያ ሰራዊቱ ጎን እንዲቆሙ” ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ያቀረቡት፡፡
“ጁንታው ቡድን የክልሉን ልዩ ሃይል በረሃብና በጥማት ውስጥ አስገብቶ በጦርነት እየማገደው ይገኛል” ያሉም ሲሆን “የልዩ ሃይል አባላቱ ለተሸነፈ ሃይል ህይወታቸውን መስዋዕት እንዳያደርጉ” አሳስበዋል፡፡
ልዩ ሃይሉ “ከፌደራል መንግስት የተሰጠውን ዕድል በመጠቀም በሚቀጥሉት 2 እና 3 ቀናት እጁን ለሃገር መከላከያ ሰራዊት እንዲሰጥ” ሲሉም ዶ/ር ዐቢይ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በትግራይ ቴሌቪዥን መግለጫን የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደብረጽዮን ገብረ ሚካዔል (ዶ/ር) ለተፈጠረው ችግር መፍትሄው “ፖለቲካዊ” ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“የአምባገነኖቹ አብይና ኢሳያስ ትግራይን ለማንበርከክ በከፈቱት ጦርነት ከ10ሺ በላይ ወታደሮች ተማርከዋል”ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የተከዜ ኃይል ማመንጫ ግድብ በመንግስት ኃይሎች መመታቱንም ገልጸዋል፡፡
ሆኖም በጊዜያዊነት የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድፖስቱ የግድቡ የመመታት ዜና ሃሰት መሆኑን አስታውቋል፡፡
በፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት በትግራይ ብሔራዊ ክልል የሚቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር አስመልክቶ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በጸደቀው ደንብ መሠረት ዶ/ር ሙሉ ነጋ በክልሉ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው መሾማቸው ይታወሳል።