ግጭቱ ከተጀመረ በኋላ ህወሓት ለፖለቲካዊ መፍትሄ ፍላጎቱን ቢገልጽም የፌደራል መንግስት ህገወጦች ሳይያዙ ድርድር እንደማይኖር ገልጿል
ግጭቱ ከተጀመረ በኋላ ህወሓት ለፖለቲካው መፍትሄ ፍላጎቱን ቢገልጽም የፌደራል መንግስት ህገወጦች ሳይያዙ ድርድር እንደማይኖር ገልጿል
በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች የትግራይ ክልል መሪ ፓርቲ የሆነውን ህወሓትን የሚያወግዙ ሰልፎች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጥቅምት 24 ምሽት ህወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ማድረሱን ከገለጹ በኃላ በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የነበረው የቆየ አለመግባባት ተባብሶ ወደ ጦርነት አምርቷል፡፡
በአዳማ፣ በሞጆ፣ በምዕራብ ሃረርጌ፣ በሱሉልታ፣በዱከም፣ ለገጣፎ፣ ሰበታ፣ ሆለታና በሌሎች ቦታዎችም ህወሃትን የሚያወግዙ ሰልፎች መካሄዳቸውን የመንስግት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
ተመሳሳይ አላማ ያላቸው ሰልፎች በትናንትናው እለት በሲዳማ ክልል አዋሳ ከተማና በኦሮሚያ ክልል በአጋሮና ጂማ ከተማዎች ተካሂደው ነበር፡፡
ባለፈው ሳምንት የፌደሬሽን ምክርቤት የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ጣልቃ እንዲገባና ጊዜያዊ አስተዳዳር እንዲቋቁም ዉሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በዛሬው እለት ዶክተር ሙሉ ነጋን በትግራይ ክልል ለተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ አድርገው ሾመዋል፡፡
ግጭቱ ከተጀመረ በኋላ የትግራይን ክልል የሚመራው ህወሓት ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲኖር ፍላጎቱን ቢገልጽም የፌደራል መንግስት “የህገወጡ የህወሓት” ቡድን ህግ ፊት ሳይቀርቡ ድርድር እንደማይኖር ገልጿል፡፡
የተወካዮች ምክርቤት በትናንትናው እለት የክልሉን መሪ ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ብረሚካኤልን ጨምሮ የ39 የምክርቤት አባላትን ያለመከሰሰ መብት አንስቷል፡፡ በትናንትናው ምሽት ጠቅላይ አቃቤ ህግ በህወሓት መሪዎች ላይ የፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዝ አውጥቶባቸዋል፡፡
የፌደራል መንግስትና ከህወሓት ጋር ያለው አለመግባባት እንዴት ጀመረ?
በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል ያለው አለመግባባት የጀመረው ኢትዮጵያን ለ27 አመታት ሲመራ የነበረው ኢህአዴግ ፈርሶ ብልጽግና ፓርቲ ሲመሰረት፣ ከመስራቾቹ አንዱ የነበረው ህወሓት የውህደቱ አካል አልሆንም ባለበት ወቅት ነበር፡፡
የፌደራል መንግስት በኢትዮጵያ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምርጫ ለማካሄድ አያስችልም በማለት ምርጫ እንዲራዘም ሲያደርግ፣ ህወሓት በራሱ ክልልዊ ምርጫ አድርጎ ነበር፡፡
ህወሓት የፌደራል መንግስት ምርጫ ማካሄድ ሲገባው ከህገመንግስቱ ውጭ ነው ስልጣን ላይ ያለው ሲል ሲከስ ቆይቷል፡፡ መንግስትን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ በበኩሉ የህወሓት ምርጫ ተቀባይነት እንደሌለው ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
የፌደራል መንግስት ከሳምንታት በፊት ከትግራይ ክልል ጋር ህጋዊ ግንኙነት ማቋረጡን አስታውቆ ነበር፡፡አሁን ላይ በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል የነበረው አለመግባባት ሁኔታው ተባብሶ ወደ ግጭት ሊያመራ ችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ የፌደራል እና የክልል የጸጥታ ሃይሎች የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት እንዲጠብቁና ሰብአዊ መብትን እንዳይጥሱ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡