መንግስት ስድስት የአማራ ክልል ከተማዎች ከታጣቂዎች ስጋት ነጻ ሆነዋል አለ
ከተሞቹ በአጭር ጊዜ ወደ ተሟላ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ ይደረጋል ተባለ
ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ እስከ ነሐሴ 17፤ 2015 የሚቆይ የሠዓት እላፊ ገደብ ጣለ
መንግስት በአማራ ክልል ያወጀውን አስቸኳይ ጊዜ ዋጅ ለማስፈጸም የተቋቋመው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ስድስት ከተሞች ከጸጥታ ስጋት ነጻ መሆናቸውን አስታውቋል።
እዙ ባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃን፣ ላሊበላ፣ ጎንደርና ሸዋ ሮቢት አካባቢዎች "አጥፊ" ሲል ከገለጻቸው ታጣቂዎች ወደ "ሰላማዊ ሁኔታ" መመለሳቸውን አስታውቋል።
ዕዙ በስድስቱ ከተሞች የነበሩ ታጣቂዎች ላይ "እርምጃ" እንደወሰዱባቸው ተናግሯል።
በአሁኑ ሰዓት ከተሞቹ ከስጋት ነጻ መሆናቸውን ሲል ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ አስታውቋል።
ጽንፈኞች ያላቸው ታጣቂዎች በአንዳንድ አካባቢዎች ወደ ቅርስ ቦታዎችና የእምነት ተቋማት በመግባት ለመደበቅ እየሞከሩ ነውም ብሏል።
ከተሞቹ በአጭር ጊዜ ወደ ተሟላ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ ይደረጋልም ተብሏል።
የጠቅላይ መምሪያ ዕዙ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሰጠኝ ስልጣን እስካሁን 14 ተጠርጣሪዎችን በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር አውያለሁ ብሏል።
ከተሞቹን ከታጣቂዎች ነጻ ማውጣት ዕቅዱ የሆነው የመጀመሪያ ምዕራፍ መጠናቀቁን ያሳወቀው ዕዙ፤ ትእዛዞችና እግድ አውጥቷል።
ከሀሙስ ነሀሴ 04 ጀምሮ በስድስቱ ከተሞች የአውሮፕላን በረራን ጨምሮ የትራንስፖርት አገልግሎቶችይጀመራሉ ብሏል።
የመንግስት፣ የንግድ፣ የጤና፣ የፋይናንስ ተቋማትም አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል ሲል መግለጫው አክሏል።
ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ በስድስቱም ከተሞች እስከ ነሐሴ 17፤ 2015 የሚቆይ የሠዓት እላፊ ገደብ መጣሉን አስታውቋል።
የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ከሚሰጡ ተሽከርካሪዎች፣ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ሰጪ ባለሞያዎች እና የጸጥታ አስከባሪ ተቋማት ባልደረቦች ውጪ ለማንኛውም ሰው እና ተሽከርካሪ ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው ብሏል።
ከዕዙ ፈቃድ ውጪ የአደባባይ ስብሰባ፣ ሰልፍ እና መሰል እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ፈጽሞ ተከልክሏል።
በማንኛውም መልኩ የህዝብ እንቅስቃሴን የሚያስተጓጉል እና የትራንስፖርት አገልግሎትን የሚያሰናክል ድርጊት "በጥብቅ የተከለከለ ነው"።
በክልሉ ከህግ አስከባሪ አካላት እና ከፈቃድ ውጭ የጦር መሳሪያ ይዞ መዘዋወር ፈጽሞ ተከልክሏል።
በስድስቱ ከተሞች የባጃጅ እና የሞተር ሳይክል እንቅስቃሴ ከነሐሴ 04 እስከ ነሀሴ 17፤ 2015 ዓ.ም ድረስም ተከልክሏል።
የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከነሀሴ 04 ጀምሮ ወደ ስራ የመመለስ እና አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አለባቸውም ተብሏል።
ዕዙ ያወጣቸውን ትእዛዞችና ክልከላዎችን በሚጥሱ ላይ ኃይልንና ሌሎች አግባብነት ያላቸውን እርምጃዎችን እንዲወስዱ ለሁሉም የህግ አስከባሪ አካላት ጥብቅ መመሪያ ሰጥቻለሁ ብሏል።
ባለፈው ሚያዚያ ወር መንግስት የክልል ልዩ ኃይሎች እንዲፈርሱ እና መልሰው እንዲደራጁ መወሰኑን ተከትሎ በአማራ ክልል ተቃውሞ መነሳቱ ይታወሳል።
መንግስት ውሳኔን በማይቀበሉ አካላት ላይ "የህግ ማስከበር" ስራ በመጀመሩ በመከላከያ ሰራዊት እና በአካባቢው ታጣቂዎች ግጭቶች ተቀስቅሰው በርካታ ንጹሃን ተገድለዋል፤ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የጸጥታ ሁኔታ በመባባሱ መንግስት በክልሉ ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አውጇል።