መንግስት ግለሰቦችን በሽብር ከመጠየቅ ይልቅ ድርጅቶችን በሽብር መፈረጅ “የሽብር ወንጀል ድርጊትን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር ይቻላል” ብሏል
መንግስት“ የሀገረ መንግሥቱን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል” ተንቀሳቅሰዋል ያላቸውን ህወሓትንና ኦነግ ሽኔ በሽብርተኝነት ለመፈረጅ የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
መንግስት ህወሓትና ሽኔን በሽብርተኝነት ለመፈረጅ የውሳኔ ሃሳብ ማቅረቡን ኢቢሲ የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
የፌደራል መንግስት የትግራይ ክልልን ይመራ ከነበረው ህወሓት ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ወደ ውጊያ ያመራ ሲሆን ኦነግ ሸኔ ደግሞ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ለተፈጠሙ ግድያዎች ተጠያቂ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
መንግስት በመግለጫው በሁለቱ ድርጅቶች “ የበርካታ ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፣ አካላቸው ጎድሏል፤ እንዲሁም ንብረታቸው ወድሟል፤ ከቀዬአቸውም ተፈናቅለዋል። እነኚህ ጥቃቶች ኅብረተሰቡ ቀጣይነት ባለው ሥጋት እና ፍርሐት ውስጥ እንዲኖር በማድረግ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ፣ ዜጎች እርስ በእርስ እንዳይተማመኑ አድርጓል።”
መንግስት ለኢቢሲ እንደላከው መግለጫ ከሆነ የህወሃትና ሸኔ “ የሀገረ መንግሥቱን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል” ተንቀሳቅሰዋል ብሏል፡፡
ህወሃትና ሸኔ “ሲፈጸሙና ሲያስፈጽሙ የቆዩዋቸው የጥፋት ተግባራት የሽብር ወንጀል ተግባራት ናቸው። እነዚህ ተግባራት የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው ዐወጅ 1176/2012 አንቀጽ 3 ሥር ስለሽብር የወንጀል ድርጊት የተሰጠውን ትርጓሜ ሙሉ ለሙሉ የሚያሟሉ ተግባራት እንደሆኑ በቀላሉ ለመገንዘብ ይቻላል።”
መንግስት ግለስቦችን በሽብር ከመጠየቅ ይልቅ ድርጅቶችን በሽብር መፈረጅ “አግባብ የሽብር ወንጀል ድርጊትን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ይችላል” ብሏል፡፡