በአፍሪካ የመንግስት ሀይሎች እና ታጣቂዎች በንጹሀን ላይ የሚያደርሱት ጥቃት መጨመሩን ሂዩማን ራይትስ ዎች አስታወቀ
ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በንጹሀን ዜጎች ፣ በጤና ተቋማት ፣ በመንግስት ተቀዋሚዎች እና በሌሎችም አካላት ላይ የሚደርሰው በደል ጨምሯል ተብሏል
በግጭቶች ወቅት ከሚደርሱ ጥሰቶች ባለፈ በአህጉሪቱ የመሰረታዊ መብቶች አፈጻጸም በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን ሪፖርቱ አመላክቷል
በአፍሪካ የመንግስት ሀይሎች እና ታጣቂ ሀይሎች በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት (በደል) መጨመሩን ሂዩማን ራይትስ ዎች አስታወቀ፡፡
አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም ባወጣው ሪፖርት የአፍሪካ መንግስታት የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን፣ ተቺዎችን፣ የማህበረሰብ አንቂዎችን እና ጋዜጠኞችን በግፍ ማሰራቸውን ቀጥለዋል ብሏል።
በተጨማሪም በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እና ታጣቂ ቡድኖች ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረገ ግድያ እና ማፈናቀል ላይ እንደሚሳተፉ በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎች ትላንት ባወጣው ሪፖርት በሱዳን እና ኢትዮጵያ እየተካሄዱ በሚገኙ ግጭቶች እየደረሱ ናቸው ያላቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ አተኩሯል፡፡
“በሁለቱ ሀገራት እየተካሄደ በሚገኘው ግጭት ተፋላሚ ወገኖች እያደረሱ በሚገኙት ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ስለመገደላቸውም” ነው የገለጸው፡፡
በሱዳን በጦርነት ምክንያት 12 ሚሊየን ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን በርካታ መሠረተ ልማቶች መውደማቸውን እና ተፋላሚዎቹ ሆን ብለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ስርጭትን በማደናቀፋቸው በሱዳን ያለውን ረሃብ ማባባሱ ተነግሯል፡፡
በሌላ በኩል “በኢትዮጵያ በአማራ ክልል የመንግስት ሃይሎች በህክምና ባለሙያዎች፣ ታካሚዎች እና በጤና ተቋማት ላይ ሰፊ ጥቃት ፈጽመዋል” ብሏል ሪፖርቱ።
በተጨማሪም “በኢትዮጵያ ባለስልጣናት የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን በማገድ በጋዜጠኞች፣የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና በተቃዋሚዎች ላይ የሚደርሰውን ወከባ፣ ማስፈራርያ እና እስራት መባባስ በርካቶችን ለስደት መዳረጉን” ጠቁሟል፡፡
የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ክፍል ኃላፊ ማውሲ ሴጉን ግጭት ላይ ከሚፈጸሙ ጥቃቶች እና የመብት ጥሰቶች ባለፈ ሀሳብን በነፃነት መግለጽ ፣ የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብት ፣ ነጻ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማድረግን የመሳሰሉ የሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አፈጻጸም በአህጉሪቱ ማሽቆልቆሉን ተናግረዋል፡፡
እነዚህን መብቶች ለመጠቀም እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎች በመንግስት ሀይሎች እንደሚታፈኑ እንደሚታሰሩ አልፎአልፎም እንደሚገደሉ ተደጋጋሚ ሪፖርቶች ይደርሱናል ብለዋል ኃላፊው፡፡
በዚህ የመብት ጥሰት ኬንያ እና ኡጋንዳን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ተጠቃሽ መሆኑን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
በኮንጎ የቀጠለው ማለቂያ የሌለው የሚመስለው ግጭት፣ ሰላማዊ ሰዎች የሚገደሉበት፣ ሴቶች የሚደፈሩበት እና በተፈናቃዮች ካምፖች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ብዙ ሰዎች ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዲሰደዱ የሚያስገድድ ሁኔታን ስለመፍጠሩ ተጠቁሟል፡፡
የሂዩማን ራይትስ ዎች አዲስ አለም አቀፋዊ ሪፖርት 25 የአፍሪካ ሀገራትን ጨምሮ ከ100 በላይ ሀገራትን የሰብአዊ መብት አያያዝ ገምግሟል፡፡