የእስራኤል ካቢኔ የጋዛውን ተኩስ አቁም ለማጽደቅ በዛሬው ዕለት ይሰበሰባል
ሀማስ እና እስራኤል 15 ወራት የዘለቀውን የጋዛውን ጦርነት ለማቆም መስማማታቸው ይታወሳል
ስምምነቱን የተቃወሙ እስራኤላውያን ትላንት የተቃውሞ ሰልፍ ሲያርጉ አንዳንድ ሚኒስትሮች ደግሞ ከሀላፊነታቸው ለመልቀቅ እየዛቱ ነው
የእስራኤል ካቢኔ የጋዘውን ጦርነት ለማስቆም ከሀማስጋር የተፈረመውን የተኩስ አቁም እና ታጋቾችን የመልቀቅ ስምምነት ለማጽደቅ በዛሬው ዕለት እንደሚሰበሰብ ተሰምቷል፡፡
በሀገሪቱ ሚኒስትሮች መካከል በስምምነቱ ዙሪያ ያለው መከፋፈል ለስምምነቱ ፊርማ መዘግየት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡
ነገር ግን ስብሰባው ትላንት ከተያዘለት ቀጠሮ ወደ ዛሬ የተዘዋወረው በሀማስ ምክንያት ነው ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ኮንኗል፡፡
አንዳንድ ሚኒስትሮች ጦርነቱ የያዘውን እቅድ ገና አላሳካም ፣ በዚህ ሁኔታም መቆም የለበትም በሚል ይህ ስምምነት የሚጸድቅ ከሆነ ከሀላፊነታቸው እንደሚነሱ እየዛቱ ነው፤ ይህ በእንዲህ እንዳለ በትላንትናው እለት በእስራኤል ተኩስ አቁሙን የተቃወሙ ሰልፎችም ተካሄደዋል፡፡
ሙሉ የመንግስት ካቢኔ ከመሰብሰቡ በፊት በዛሬው ዕለት የደህንነት ካቢኔው በተኩስ አቁም ስምምነቱ ዙሪያ የሚመክር ሲሆን ቀጥሎም ለሙሉ ካቢኔው እንዲጸድቅ ይቀርባል፡፡
ነገር ግን ስምምነቱን የሚያጸድቀው ሙሉ ካቢኔ ዛሬ ወይም ነገ መች እንደሚሰበሰብ እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በኳታር በነበሩ ተደራዳሪዎች በይፋ የተፈረመው ዋናው ስምምነት ግን የተኩስ አቁሙ ከመጪው ዕሁድ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ያስቀምጣል፡፡
የኋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ጆን ከርቢ “ስምምነቱ ረጅም ጊዜ የተለፋበት እና ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለውጤት የቀረበ ነው፤ ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ የሚመልሰው መሰናክል ያጋጥመዋል ብየ አላስብም” ብለዋል፡፡
እስራኤል በጋዛ የምታርገውን መጠነ ሰፊ ጥቃት አሁንም የቀጠለች ሲሆን የተኩስ አቁሙ ከተነገረ በኋላ በአንድ ቀን ውስጥ 86 ንጹሀን መሞታቸውን የፍልስጤም ባለስልጣናት አሳውቀዋል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው በስምምነቱ ዙሪያ ያልተጠናቀቁ ጉዳዮች በፍጥነት እንዲቋጩ ታጋቾች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ እና የ15 ወራቱ ጦርነትም እንዲቆም ጥሪ አድርገዋል፡፡
እስራኤል በተደራዳሪዎቿ በኩል በኳታር የፈረመችው ስምምነት በደህንነት ካቢኔው እና በመንግስት እስከሚጸድቅ ድረስ ስራ ላይ አይውልም ፡፡
አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እሁድ ተግባራዊ ለማድረግ የታቀደው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እስከ ቅዳሜ ድረስ የመጨረሻ ይሁንታ ካልሰጠች ሊዘገይ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡