የተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ምደባ ከዛሬ እኩለ ሌሊት ጀምሮ ይፋ እንደሚደረግ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ
ሚኒስቴሩ፤ ምንም አይነት ጥያቄም ሆነ ማመልከቻ እንደማይቀበል አሳውቋል
በ2014 ብሔራዊ የ12ኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱት 895 ሺህ 520 ተማሪዎች ያለፉት 3 ነጥብ 3 በመቶ ብቻ መሆናቸው ይታወቃል
የተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ምደባ ከዛሬ እኩለ ሌሊት ጀምሮ ይፋ እንደሚደረግ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ በማህበራዊ የትስስር ገጹ ላይ ባስተላለፈው መልእክት በ2014 የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ወስደው 50 ከመቶና ከዚያ በላይ ያመጡ እና መደበኛ የቅድመ ምርቅ ትምህርት ለመከታተል ያመለከቱ ተማሪዎች የተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ የካቲት 05/2015 እኩለ ሌሊት ጀምሮ ይፋ እንደሚደረግ ገልጿል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች እስከ የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ተገቢውን ዝግጅት አድርገው የመጀመሪያ ዓመት አዲስ ገቢ ተማሪዎችን የቅበላ መርሃ ግብር የሚያሳውቁ በመሆኑ ተማሪዎች አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉም ሚኒስቴሩ አሳስቧል፡፡
ሚኒስቴሩ ተማሪዎች በዌብሳይት: https://result.ethernet.edu.et ፤SMS: 9444፣ ቴሌግራም ቦት: @moestudentbot አማካኝነት የተመደቡበትን ተቋም ማወቅ ይችላሉም ብሏል፡፡
ከምደባ ጋር ተያይዞ ላሉ ማንኛውም ጥያቄ፡-result.ethernet.edu.et ላይ በመግባት "Complaint" የሚለውን በመጫን ጥያቄዎችን ማቅረብ እንደሚችሉም ነው የሚኒስቱሩ መረጃ የሚያመለክተው፡፡
በተጨማሪም ምንም አይነት ጥያቄም ሆነ ማመልከቻ በአካል እንደማይቀበል አሳውቋል ሚኒስቴሩ፡፡
በ2014 ብሔራዊ የ12ኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱት 895 ሺህ 520 ተማሪዎች 350 እና ከዛ በላይ ውጤት ያመጡት 29 ሺህ 900 ወይም 3 ነጥብ 3 በመቶ ብቻ መሆናቸው አይዘጋም፡፡
ከነዚህም በአማካይ ከ50 በመቶ በላይ ያመጡት ከተፈጥሮ ሳይንስ 22 ሺህ እንዲሁም ከማህበራዊ ሳይንስ 6 ሺህ 973 ተማሪዎች መሆናቸውም ይታወቃል፡፡