ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ የ8ኛ እና የ12 ክፍል የገጽ ለገጽ የማካካሻ ትምህርት ተጀምሯል
የትምህርት ሚኒስትሩ ማስተማር ጀመሩ
ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ የ8ኛ እና የ12 ክፍል የገጽ ለገጽ የማካካሻ ትምህርት መስጠት ተጀምሯል።
የመማር ማስተማር ስራውን የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዳግማዊ ሚንሊክ መሰናዶ ትምህርት ቤት በመገኘት ትምህርት በይፋ አስጀምረዋል።
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለተማሪዎች የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ሲያደርጉ
የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂነር) በትምህርት ቤቱ ተገኝተው የመምህራንን ጫና ለመቀነስ “እኔም አስተምራለሁ” በሚል መፈክር በተጀመረው ንቅናቄ መሰረት የማስተማር ስራ ጀመሩ፡፡
ሚኒስትሩ በዳግማዊ ምንሊክ መሰናዶ ትምህርት ት/ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን የፊዚክስ ትምህርት በማስተማር ጀምረዋል፡፡ በትምህርት ቤቱ በሚወጣ መርሃ ግብር መሰረትም ለ45 ቀን የማስተማር ስራውን እንደሚያከናውኑ አስታውቀዋል፡፡
ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት የዛሬ ዓመት በዓለም “በመንግስት የዲጂታል አሰራር ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ” በሚል በውድድሩ ከተሳተፉ 500 እጩዎች መካከል 100 ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ሲመረጡ አንዱ ሆነው ተመርጠዋል፡፡ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በዲጂታላይዜሽን፣ በመረጃ ደህንነት፣ በዲጂታል መታወቂያ እና በመሳሰሉት የዲጂታል አሰራር ስርዓቶች ውስጥ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር የውድደሩ መስፈርቶቹ ነበሩ፡፡
ዶ/ር ኢንጅነር ጌታሁን የካቢኔ አባል ሆነው የተሾሙት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ዘመን ነበር፡፡ የአሁኑ የትምህርት ሚኒስትር ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩጥ መምህርም ነበሩ፡፡
“እኔም አስተምራለሁ” በሚል መፈክር ፣ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተቋርጦ የቆየው ትምህርት በሚጀመርበት ጊዜ ጡረታ የወጡ መምህራንን ጨምሮ ክህሎቱ ያላቸው ሁሉ የመማር ማስተማር ስራውን እንዲያግዙ ከዚህ ቀደም የትምህርት ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል፡፡
ከአ/አ በተጨማሪ በመላ ሀገሪቱም ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት 45 ቀናት የ8ኛ እና የ12 ክፍል የማካካሻ ትምህርት እንደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡
ተማሪዎች ከጤና ባለሙያዎች እንዲሁም መምህራን የሚሰጣቸውን ምክር እና አቅጣጫ በአግባቡ እንዲተገብሩ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አሳስበዋል።