ዚዳንን የዘለፉት የፈረንሳይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት በጾታዊ ትንኮሳ ምርምራ እየተደረገባቸው ነው
ዚዳንን የዘለፉት የፈረንሳይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት በጸታዊ ትንኮሳ ምርምራ እየተደረገባቸው ነው
ፕሬዝዳንቱ ክስ የተመሰረተባቸው የእግር ኳስ ወኪል በሆነችው ሶንያ ሱይድ ላይ ጾታዊ ትንኮሳ ፈጽመዋል በሚል ነው
የፓሪስ አቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት በጾታዊ ትንኮሳ ተጠርጥረዋል በተባሉት አዛውንቱና አነጋገሪው የፈረንሳይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኖኤል ሌ ግሬት ላይ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።
ምርመራው የተከፈተው የእግር ኳስ ወኪል ሶንያ ሱይድ በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ፈረንሳይ በአርጀንቲና ከተሸነፈች ከሳምንታት በኋላ በግሬት ላይ ላይ ክስ ከመሰረተች በኋላ ነው።
ሶንያ ሱይድ፥ ሌ ግሬት "በአፓርታማው ውስጥ ስንገኛኝ በግልጽ ጠይቆኛል" ስትል አር ኤም ኤስ ለተባለ ሬዲዮ ጣቢያ ተናግራለች፡፡
የሱይድን ክስ መነሻ በማድረግ የፈረንሳይ ስፖርት ሚኒስቴር ባደረገው አጠቃላይ ግምገማ ሌ ግሬት ላይ በዓቃቤ ህግ አማካኝነት የጾታዊ ትንኮሳ ክስ ቢያቀርብም ሌ ግሬት ውንጀላውን ውድቅ አድርገውታል፡፡
ይሁን እንጅ በፕሬዝዳንቱ ላይ የቀረበው ክስ ባለፈው ሳምንት በፈረንሳዩ ኮከብ ዚነዲን ዚዳን ላይ ከሰነዘሩት አስደንጋጭ አስተያየት ጋር ተዳምሮ ከስራቸው “አንድ እርምጃ ገለል እንዲሉ” ተድረገው በምትካቸው ፊሊፕ ዲያሎ በጊዜያዊ ፕሬዝዳንትነት እየሰሩ ስለመሆናቸው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ፌዴሬሽኑን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
እንደፈረንጆቹ ከ2011 ጀምሮ የፈረንሳይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት ሌ ግሬት ፤ ሰሞኑን በዚነዲን ዚዳንና በካሪም ቤንዜማ ላይ በሰነዘሩት ክብረ-ነክ አስተያየት የዓለም መነጋገሪያ ሆነው መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡
ፕሬዝዳንቱ በተለይም የፈረንሳይ ብርቅዬ ልጅ ተድረጎ የሚቆጠረውን የእግር ኳስ ጠቢቡ ዚነዲን ዚዳንን የአስተዳደር ችሎታን በይፋ ካወገዙ በኋላ በፈረንሳይ ሚዲያ ትርምስ ማስነሳቱ እየተነገረ ነው፡፡
ሌ ግሬት ስለ ዚዳን የማኔጅመንት ብቃት ተጠይቀው ሲመልሱ "ዚዳን? ... ታዲያ እኔ ስለዚዳን ምን አገባኝ? የፈለገውን ማድረግ ይችላል፤ እስከዛሬ ሊያገኘኝ አልሞከረም፤ ለነገሩ ቢደውልልኝም የሱን ስልክ አላነሳም" ማለታቸው ነበር አነጋጋሪው ጉዳይ።
የፕሬዝዳንቱ ያልተጠበቀ አስተያየት በዚዳን ብቻ ያበቃ አልነበረም፤ በወቅቱ የባላንዶር አሸናፊው ካሪም ቤንዜማ ዙሪያም ያልተጠበቀ ነገር ተናግረዋል፡፡
"ቤንዜማ? ቤንዜማ በዓለም ዋንጫው ላይ አልነበረም፤ እና ምን ይፈጠር? እንዳውም እንኳንም አልኖረ፤ እሱ ቢኖር ኖሮ ጅሩድ አይካተትም ነበር፤ ይሄ ደግሞ በዓለም ዋንጫው ያስቆጠርናቸውን በርካታ ጎሎች ያሳጣን ነበር" ያሉበት አጋጣሚ በርካቶችን ያስገረመ ነበር፡፡
ፈረንሳዊው የ81 ዓመት አዛውንት ሌ ግሬንት ፈረንሳይ በምትመካባቸው ኮከቦች ዙሪያ የሰጡት አስተያየት ታዲያ በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የሀገሪቱ የስፖርት ሚኒስትር አሜሊ ኦዲያ ካስቴራ ጭምር ተወግዟል፡፡
ፕሬዝዳንቱ እና ሚኒስትሯ፤ ሌ ግሬት ለአወዛጋቢ ንግግራቸው ይቅርታም ጭምር እንዲጠይቁ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው።
በጥያቄው መሰረትም ሌ ግሬት ላልተገባ ንግግራቸው ይቅርታ ጠይቀው ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርጓል፡፡
የፈረንሳይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለተፈጠረው ስህተት የእርምት መግለጫ እስከማውጣት ደርሷል፡፡