ብሪታኒያ በጎዳና ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ትንኮሳን በእስር ልትቀጣ ነው
በወጣው ሕግ መሰረት ጾታዊ ትንኮሳ እስከ ሁለት አመት የሚደርስ እስራት ያስቀጣል
32 በመቶ የሚሆኑ የብሪታኒያ ሴቶች አመሻሽ ላይ በመንገድ ሲጓዙ ምቾት እንደማይሰማቸው ጥናቶች ያስረዳሉ
ብሪታኒያ በጎዳና ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ትንኮሳዎችን እስከ ሁለት አመት በሚደርስ እስር ልትቀጣ መሆኑ አስታወቀች፡፡
የሀገሪቱ የውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር እንደገለጸው ከሆነ በመንገድ ላይ ማንኛውንም ሰው መተንኮስ፣ መከታተል ይሁን መንገድ መዝጋት ፣ መሳደብ፣ ማስፈራራት እንዲሁም ተመሳሳይ ድርጊቶች መፈጸም በሕግ ያስቀጣል፡፡
በሌበር ፓርቲ ተቀባይነት አግኝቶ በፓርላማ አባሉ ቶሪ ግሬግ ክላርክ ለፓርላማ የቀረበው ሕግ የሴቶችን መብት ለማስከበር የሚያስችል ጥሩ እርምጃ ነው ተብሏል፡፡
ሕጉን አጥብቀው ከሚደግፉት አንዷ የሆኑት የፓርላማ አባሏ ሰኤላ ብሬቨርማን “ሁሉም ሴቶች መንገድ ላይ በሚጓዙበት ወቅት ደህንነት ሊሰማቸው ይገባል” ብለዋል፡፡
“በሕጉ መሰረት ጾታዊ ትንኮሳ የሚፈጽሙ አካላት የሚገባቸውን ቅጣት የሚያገኙ ይሆናል” ሲሉም አክለዋል ሰኤላ ብሬቨርማን፡፡
በብሪታኒያ ቀድሞውንም ቢሆን ጾታዊ ትንኮሳ በሕግ እንደሚያስቀጣ ቢታወቅም፤ የአሁኑ ሕግ በጎዳናዎች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ትንኮሳ ራሱን የቻለ ወንጀል ሆኖ እንዲወጣ የሚያስችልና የወንጀሉ ሰለባ የሚሆኑ ሴቶች በቀላሉ ለፖሊስ እንዲያመለክቱ የሚያበረታታ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ፤ 32 በመቶ የሚሆኑ የብሪታኒያ ሴቶች አመሻሽ ላይ በመንገድ ሲጓዙ ምንም አይነት ምቾት አይሰማቸውም፡፡
እድሜያቸው ከ34 አመት በታች የሆኑ ሴቶች ለጾታዊ ትንኮሳ ተጋላጭ የመሆን እድላቸው ከፍተኛ ቢሆንም፤ ያጋጠማቸውን ችግር ወደ ፖሊስ ሄደው የማሳወቁ እድል ዝቅተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡
በተለይም ባለፈው አመት አንዲት ሳራ ኤቨርድ የተባለች እንስት በደቡብ ለንደን አከባቢ በፖሊሶች ታፍና መሞቷን ተከትሎ ሴቶች በፖሊስ ላይ ያላቸውን እምነት ጥያቄ ውስጥ የከተተ አጋጣሚ እንደሆነ ይነሳል፡፡