11 ጊዜ ጾታዊ ጥቃት ፈጽመዋል የተባሉ ወንጀለኞች መለቀቃቸው የስፔን ሴቶችን አስቆጣ
የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር "በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጾታዊ ጥቃት በየቀኑ የሚያሳፍረን አሳዛኝ እውነታ ነው” ብለዋል
በስፔን እንደፈረንጆቹ ከ 2003 ጀምሮ 1ሺህ 171 ሴቶች በጾታዊ ጥቃት ምክንያት ህይወታቸው አልፈዋል
በሺህ የሚቆጠሩ ስፔናውያን በማድሪድ እና በባርሴሎና በጎዳናዎች ላይ በመውጣት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡
በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለማስወገድ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ ቀን ምክንያት በማድረግ ትናንት አመሻሽ ላይ በማድሪድ መሃል በሚገኘው ግራን ቪያ ወርደው የተለያዩ መልእቶች የያዙ ባነሮችን ይዘው ድምጻቸው ሲያሰሙ ታይተዋል፡፡
“ ጾታዊ ጥቃት ይቁም” እና “እኛ ሴቶች እቃዎች አይደለንም” የሚሉ መፈክሮች ሲያሰሙም ተደመ፣ጠዋል ሰልፈኞቹ፡፡
የ42 ዓመቷ መምህር ና የማድሪድ ነዋሪ ሱሳና ሪታ “እዚህ የመጣሁት በጾታ ጥቃት ችግር፣ በሚከሰቱት ሁሉም ሞት፣ በሴቶች ላይ በሚደርስ በደል ምክንያት ነው…” ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሰልፉን ተከትሎ በሶሻሊስት ፓርቲ ዝግጅት ላይ ሳሉ ንግግር ያደረጉት የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ “ወንዶች ማቺስሞ (ሴቶችን ዝቅ አድርጎ የማየት ዝንባሌ) ማቆም አለባቸው” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
"ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጾታዊ ጥቃት በየቀኑ የሚያሳፍረን አሳዛኝ እውነታ ነው" ሲሉም ነው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስተሩ፡፡
በስፔን እንደፈረንጆቹ ከ 2003 ጀምሮ 1ሺህ 171 ሴቶች በጾታዊ ጥቃት ምክንያት ህይወታቸው ማለፉ የሀገሪቱ የእኩልነት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡
“በ2022 ብቻ 38 ሴቶች ሞተዋል”ብሏል ሚኒስቴሩ።
በሺዎች የሚቆጠሩ ስፔን ሴቶች ለተቃውሞ የወጡት ጾታዊ ጥቃት ፈጽመው በእስር ላይ በቆዩ አንዳንድ ወንዶች፤ ተሻሻለ በተባለው አዲስ ህግ ክፍተት በመኖሩ ምክንያት የእስር ጊዜያቸው እንዲቀንስ መደረጉን ተከትሎ ተቆጥተው እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
ይህ ብቻ አይደለም አዲሱ ህግ በፖለቲከኞች መካከል ቁጣ እና የጦፈ ክርክርም አስከትሏል።
“ኦንሊ የስ ሚንስ የስ” በመባል የሚታወቀው ህግ፣ ማንኛውንም በስምምነት ላይ ተመርኩዞ ያልተፈጸመ ጾታዊ ግንኙነት በአስገድዶ መድፈር የሚፈርጅ ቢሆንም ለወነጀሎቹ ያስቀመጣቸው ቅጣቶች ቀላል የሚባሉ መሆናቸው አነጋጋሪ ሆነዋል፡፡
ቢያንስ 11 ጾታዊ ጥቃት ፈጽመዋል የተባሉ ወንጀለኞች የእስር ጊዜያቸው የተቀነሰ ሲሆን አምስት ወንዶች ደግሞ ከእስር ቤት መለቀቃቸውን የሮይተረስ ዘገባ ያመለክታል፡፡