የ2014ዓ.ም “ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ” በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ተራዘመ
አዘጋጁ ወድድሩ ለመቼ እንደተራዘመ ግልጽ አላደረገም
ውድድሩ ህዳር 5 ቀን እንደሚካሄድ ቀን ተቆርጦለት እንደነበረ አዘጋጁ አስታውቋል
የ2014ዓ.ም ቶታልኢነርጂስ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ መራዘሙን አዘጋጁ አስታውቋል፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት ህዳር 5 ቀን ሊካሄድ የነበረውን የ2014 ቶታልኢነርጂስ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን የውድድሩ አዘጋጅ በድረገጹ አስታወቋል፡፡
የተራዘመው ውድድር ለመቼ እንደተራዘመ ያላሳወቀው ተቋሙ የውድድሩን ተለዋጭ ቀን በቅርብ ሳምንታት ውስጥ የምናሳውቅ ይሆናል ብሏል፡፡
ከትናንት በስትያ በኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክርቤት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በዛሬው እለት በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቀርቦ በአብጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተመሰረተው ሻለቃ አትሌት ገብረስላሴ ሲሆን በየአመቱ በሚካሄደው በዚህ ሩጫ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሳተፉበት ነበር፡፡
አዋጁ የታወጀው በሀገር የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ በመደቀኑና፤ ይህንንም አደጋ በመደበኛ ሁኔታ መቆጣጠር ባለመቻሉ የጸጥታና የደህንነት ተቋማትንና ዜጎችን በማቀናጀት አደጋውን ለመቀልበስ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር ለማድረግ መሆኑን የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዴዎን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
አዋጁን የሚያስፈጽመው “የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ዕዝ” ሲሆን ይህም የሚመራው በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ስር እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ ይህ ዕዝም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ (ለጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ) እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
ዕዙ የሀገሪቱን ሁሉንም የጸጥታ አካላት ማዘዝና ማንቀሳቀስ እንደሚችል ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም የተቋቋመው ዕዝ ማንኛውንም መሳሪያ የታጠቀ አካልን የማዘዝና የማሰማራት ስልጣን እንደተሰጠው ጌዲዎን ጢሞቲዮስ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴሩ፤የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፎ የተገኘ ሰው፤ ቀላለ ወንጀል ከሆነ እስከ ሶስት አመት የሚያስቀጣ ሲሆን ከባድ ወንጀል ከሆነ ደግሞ እስከ 10 አመት የሚፈጅ እስራት እንደሚያስቀጣ አስታውቋል፡፡