ስለግሪንሃውስ ጋዞች ልናውቃቸው የሚገቡ ጉዳዮች
የግሪንሃውስ ጋዞች ለምድር ሙቀት መጨመር ያላቸው ድርሻ ምንድን ነው?
የግሪንሃውስ ጋዞች በተፈጥሯዊ መንገድና በሰው ልጆች የየእለት እንቅስቃሴ ወደ ከባቢ አየር ይቀላቀላሉ
የግሪንሃውስ ጋዞች የምድራችን ሙቀት በአማካይ ከ14 ዲግሪ ሴልሺየስ በታች እንዳይሆን ያደርጋሉ።
እነዚህ ጋዞች በከባቢ አየር ላይ ባይኖሩ የምድር ሙቀት ወደ -18 ዲግሪ ሴልሺየስ ሊወርድ እንደሚችልም ነው የሚነገረው።
የሰው ልጆች እንቅስቃሴ የግሪንሃውስ ጋዝ መጠንን በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ማድረጉ ግን የአለምን ሙቀት በየጊዜው እንዲያድግ እያደረገ ነው።
ከኢንዱስትሪ አቢዮት አንስቶ የሰው ልጅ ወደ ከባቢ አየር የሚለቃቸው የግሪንሃውስ ጋዞች እየጨመረ መሄዱን የሚያነሱ ተመራማሪዎች ባለፉት ሶስት አስርት አመታት ለታየው ፈጣን የሙቀት መጨመር ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ያብራራሉ።
የግሪንሃውስ ጋዞች በተፈጥሯዊ መንገድ (እንሰሳት እና አትክልቶች የአተነፋፈስ ስርአት ጋር በተያያዘ) የሚለቀቁ አልያም በሰው ሰራሽ መንገድ ወደ ከባቢ አየር የሚቀላቀሉ (ከፋብሪካዎች እና ተሽከርካሪዎች ናቸው።
የግሪንሃውስ ጋዞች የሚባሉት የትኞቹ ናቸው?
1. ካርበንዳይ ኦክሳይድ (CO2)
በከባቢ አየር ውስጥ ያለው የካርበን ዳይኦክሳይድ መጠን በ1800ዎቹ ከተጀመረው የኢንዱስትሪ አቢዮት በኋላ በ50 በመቶ ጨምሯል።
ለዚህም የሰው ልጅ ምግብ ለማብሰል ከሰል መጠቀሙና ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋ መፈጸሙ በምክንያትነት ይጠቀሳል። ከኢንዱስትሪዎች የሚለቀቀው የካርበን ዳይኦክሳይድ መጠን እያደገ መሄድም ለከባቢ አየር መበከል ትልቁን ድርሻ ይይዛል።
2. ሚቴን (CH4)
የከብት እርባታ፣ የሩዝ እርሻ፣ ባህላዊ የነዳጅ እና ጋዝ ማውጣት ስራ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን የሚቴን መጠን ይጨምራል። ይህም ለአለም የሙቀት መጨመር አንዱ መንስኤ ተብሎኦ ይጠቀሳል።
3. ናይትረስ ኢክሳይድ(N2O)
ናይትረስ ኦክሳይድ የፋብሪካ እና ሰው ሰራሽ ማዳበሪያዎችን በስፋት ጥቅም ላይ ሲውል እና ባዮማስ ሲቃጠል ነው ከባቢ አየርን የሚቀላቀለው።
4. የውሃ ትነት
የውሃ ትነት በከባቢ አየር በብዛት የሚገኝ የግሪንሃውስ ጋዝ ሲሆን የባቢ አየር ሙቀት እንዲጨምር ያደርጋል። ይሁን እንጂ እንደ ካርበን ዳይኦክሳይድ በከባቢ አየር ለመቶ አመታት አይቆይም፤ የውሃ ትነት እድሜ ከቀናት አያልፍም።
እንደ ሃይድሮፍሎሮካርቦን (HFC)፣ ፐርፍሎሮካርቦን (PFC) እና ሰልፈር ሄክሳፍሎራይድ (SF6) ያሉ ከኢንዱስትሪዎች የሚለቀቁ የግሪንሃውስ ጋዞችም የምድርን ሙቀት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ማድረጋቸው ነው የሚነገረው።
የግሪንሃውስ ጋዞች ለአየር ንብረት ለውጥ ያላቸው ድርሻ እና እንዴት እንቆጣጠረው በሚለው ዙሪያ የተለያየ ሃሳብና አረዳድ ያላቸው ሳይንቲስቶች ሙግት ቀጥሏል።
አብዛኞቹ ተመራማሪዎች ግን በታዳሽ የሃይል አማራጭ ላይ በስፋት መስራትና በካይ ጋዞችን የሚለቁትን ከአገልግሎት ማስወጣት ዋነኛው የመፍትሄ አቅጣጫ መሆኑን ያምኑበታል።