የግግር በረዶ መቅለጥ ከተሞችን ከምድረ ገጽ ሊያጠፋ እንደሚችል ተገለጸ
80 በመቶ የግሪንላንድ መልክዓ ምድር በበረዶ ግግር የተሸፈነ ነው
ግሪንላንድ በየዓመቱ 234 ቢሊዮን ቶን ግግር በረዶዋን እያጣች ትገኛለች
የግሪንላንድ ግግር በረዶ መቅለጥ ከተሞችን ከምድረ ገጽ ሊያጠፋ እንደሚችል ተገለጸ፡፡
በአትላንቲክ እና አርክቲክ ውቂያኖሶች መካከል የምትገኘው ግሪንላንድ የአየር ንብረት ለውጥ በህልውናዋ ላይ አደጋ መደቀኑ ተገልጿል፡፡
ግሪንላንድ በሙቀት መጨመር ምክንያት ግግር በረዶዋ እየቀለጠ እና የወንዞቿን መጠን እንዲጨምሩ በማድረግ ከተሞች በውሃ መጥለቅለቅ እንዲጠቁ በማድረግ ላይ ነው ተብሏል፡፡
ሀገሪቱ ካላት አጠቃላይ መልክዓ ምድር ውስጥ 80 በመቶው በግግር በረዶ የተሸፈነ ሲሆን በየጊዜው ይህ ግግር በረዶ እየቀለጠ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
እንደ አማዞን ጥቅጥቅ ደን ምድራችን ተስማሚ ከባቢ አየር እንዲኖራት በማድረግ የማይተካ ሚና አለው የሚባለው አርክቲክ ግግር በረዶ ሲሆን ይህም በሙቀት መጨመር ምክንያት በፍጥነት እየቀለጠ ነው ተብሏል፡፡
በአጠቃላይ በምድራችን ሙቀት ምክንያት ከሚፈጠረው በረዶ ይልቅ የሚቀልጠው በረዶ መጠን እንደሚበልጥ ሲገለጽ በግሪንላንድ ብቻ በየዓመቱ 234 ቢሊዮን ቶን ግግር በረዶ በመቅለጥ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
አሁን ላይ በየዓመቱ የሚቀልጠው የግግር በረዶ መጠን በፈረንጆቹ ከ1990 ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ7 እጥፍ ጨምሯልም ተብሏል፡፡
የዓለም ግግር በረዶ መቅለጥ በወደቦች እና ብህር ዳርቻዎች አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን ህይወት ከመጉዳቱ ባለፈ የብዝሃ ህይወት ውድመትንም እንደሚያስከትል ተገልጿል፡፡