የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት አለም ከዩክሬን ፊቱን እንዲያዞር አድርጓል - ዜለንስኪ
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ምዕራባውያን ሀገራት ለኬቭ ፈጣን ወታደራዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል
ዜለንስኪ የሀገራቸው ጀነራል ጦርነቱ ወደ መቆም ተቃርቧል ማለታቸውንም አስተባብለዋል
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት አለም ከዩክሬን ፊቱን እንዲያዞር አድርጓል አሉ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ።
ፕሬዝዳንቱ በኬቭ ጉብኝት እያደረጉ ከሚገኙት የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደርላይን ጋር በሰጡት መግለጫ ሩሲያ ለዩክሬኑ ጦርነት የሚሰጠው ትኩረት እንዲደበዝዝ ትሻለች ብለዋል።
ዜለንስኪ የሀገራቸው ጀነራል የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ወደመቆም ተቃርቧል ማለታቸውንም አስተባብለዋል።
የዩክሬን ጦር ዋና አዛዥ ቫለሪ ዛሉዥኒ በቅርቡ በሰጡት አስተያየት ጦርነቱ መቀዛቀዙንና ይህም ሞስኮ ጦሯን ዳግም እንድታደራጅ ያግዛታል ማለታቸው የሚታወስ ነው።
“ሁሉም ደክሞታልና የተለያየ አስተያየት ሊሰጥ ይችላል፤ ነገር ግን ጦርነቱ አልቆመም” ያሉት ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ የሩሲያን የአየር ሃይል የበላይነት ግን አልሸሸጉም።
ኬቭ አሜሪካ ሰራሽ ኤፍ -16 የጦር አውሮፕላኖች እና ዘመናዊ የአየር መቃወሚያዎች በፍጥነት ያስፈልጋታል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የዜለንስኪ ንግግር ምዕራባውያን ሀገራት በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ምክንያት ለዩክሬን ፈጣን ድጋፍ እያደረጉ አይደለም የሚል አንድምታ ያለው ነው ብለዋል ተንታኞች።
ዩክሬን በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል የጀመረችው የመልሶ ማጥቃት እርምጃ እስካሁን የሚፈለገውን ውጤት አላስመዘገበም።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም የዩክሬን መልሶ ማጥቃት መክሸፉን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል።
የመከላከያ ሚኒስትራቸው ሰርጌ ሾጉ ግን ኬቭ በአውደ ውጊያ እየተሸነፈች ቢሆንም ከኔቶ አጋሮቿ አዳዲስ የጦር መሳሪያ ድጋፍ አግኝታለች ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
የብሪታንያ የመከላከያ ደህንነት ያወጣው ሪፖርት በበኩሉ ሩሲያ በዶንባስ አቪዲቭካ ከተማ ከ200 በላይ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች እንደወደመባት አመላክቷል።