ሃብቱን ለማሳየት በብር ኖቶች የአበባ ጉንጉን ያሰራው ህንዳዊ ሙሽራ
በባለ 500 ሩፒ ኖቶች የተሰራው የአበባ ጉንጉን 2 ሚሊየን ሩፒ ዋጋ አለው ተብሏል
የህንዳዊው ሙሽራ ተግባር አድናቆትና ነቀፌታ ገጥሞታል
በሰርጉ እለት ሃብቴን እዩልኝ ያለው ህንዳዊ በማህበራዊ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆኗል።
ግለሰቡ በባለ 500 ሩፒ ኖቶች የተሰራ የአበባ ጉንጉን አድርጎ ታይቷል።
የኖቶቹ ብዛት የአበባ ጉንጉኑን ዋጋ 2 ሚሊየን ሩፒ ያደርሰዋል ነው የተባለው።
ህንዳዊው ሙሽራ ከሰገነት ላይ ሆኖ ያጠለቀው በገንዘብ ብቻ የተሰራው የአበባ ጉንጉን እስከ መሬት ተዘናጥፎ ሲወርድ የሚያሳይ ምስል በኢንስታግራም መለቀቁን ተከሎም የበርካቶችን ቀልብ ስቧል።
አንዳንዶች በሃብቱ መብዛት አግራሞታቸውን ሲገልጹ፥ በርካቶች ከልክ ያለፈው ቅንጦት አላስደሰታቸውም ብሏል የህንዱ ኤንዲቲቪ።
ሌሎች ደግሞ የብር ኖቶቹ ትክክለኛ ገንዘብ አይሆኑም ሲሉ ጥርጣሬያቸውን አጋርተዋል።
ምንም እንኳን የተለያዩ አስተያየቶች ቢሰጡም በኢንስታግራም ገጽ ላይ የተለጠፈው ቪዲዮ ከ15 ሚሊየን በላይ ተመልካች አግኝቷል።
ከተሰጠቱ አስተያየቶች መካከልም “እንዴት ነው ይህን ረጅምና በገንዘብ ኖት የተሰራ የአበባ ጉንጉን አድርጎ የሚንቀሳቀሰው?” ፤ “የአበባ ጉንጉኑ እንደ ሙሽሪት ቬሎ ተጎታጅ ነው እንዴ?” እና “ለገቢዎች ቢሮ ማሳወቅ አለብን” የሚሉት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
በህንድ በተለያዩ አካባቢዎች ከገንዘብ ኖቶች የሚሰራ የአበባ ጉንጉን በሰርግ ወቅት ማድረግ የተለመደ ነው።
ሀብትን ያሳያል፤ መልካም ገድንም ይዞ ይመጣል ተብሎ የሚታመንበት ድርጊት ግን በበርካቶች ነቀፌታ ይገጥመዋል፤ የሩፒ ኖትን ለመሰል ድርጊት መጠቀምም ክልክል እንደሆነ ሲገለጽ ይደመጣል።