የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የከርሰምድር ውሀን ከጥፋት መጠበቅ የግድ ነው ተባለ
በስፔን ማድሪድ እየተካሄደ በሚገኘው 25ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ COP25 በከርሰምድር ውሀ ጥበቃ ዙሪያ አስቸኳይ ርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባ ሳይንቲስቶች አሳስበዋል፡፡
በጉባኤው ላይ የከርሰምድር ውሀ እየተመናመነ መምጣት አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱ የተነሳ ሲሆን ወደ 800 የሚጠጉ አለማቀፍ ሳይንቲስቶች ችግሩ አፋጣኝ እልባት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡
ለቀጣይ የምግብ ምርት፣ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቋቋም የከርሰምድር ውሀ አስተዋጽኦ እጅግ የጎላ እንደሆነ ነው ሳይንቲስቶቹ የገለጹት፡፡
በተለይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሀራ በታች ለሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት የከርሰምድር ውሀ የማይተካ ሚና እንዳለው ነው ሳይንቲስቶቹ የጠቆሙት፡፡
ሳይንቲስቶቹን በመወከል አለማቀፉ የውሀ አስተዳደር ተቋም ባስተላለፈው የትግበራ ጥሪ የወንዞች ደህንነትም ቢሆን ከከርሰ ምድር ውሀ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት እንዳለው አስታውቋል፡፡ የከርሰምድር ውሀ ከአለማችን የግብርና መስኖ ውሃ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሚሸፍን ሲሆን 2 ቢሊዮን ህዝብ የመጠጥ ውሀ የሚያገኘው ከዚሁ ምንጭ ነው፡፡
አስከፊ ድርቅን ለመከላከልም ድርሻው ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ በደረቃማ አካባቢዎች የሚኖሩ አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶአደሮች በዝናብ አጠር ወቅቶች የከርሰ ምድር ውሀ ጥገኞች ናቸው፡፡
99 በመቶው የአለማችን ንጹህ ውሀ የሚገኘው ከከርሰ ምድር የውሀ ምንጭ መሆኑን በመጠቆም፣ ይሁንና ከልክ ባለፈ አጠቃቀምና ብክለት በከፍተኛ ደረጃ እየተጎዳ መሆኑን ሳይንቲስቶቹ አብራርተዋል፡፡ ለዚህም የግንዛቤ እጥረት፣ የመሬት አጠቃቀም እና የአስተዳደር ችግሮች በዋና ምክኒያትነት ተጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት ረገድ ትልቅ አበርክቶ አላቸው የተባሉ 15 ፕሮጄክቶች በስፔን ማድሪድ በመካሄድ ላይ ባለው የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ተሸልመዋል፡፡ ፕሮጄክቶቹ ተጨባጭ ውጤትን ሊያስገኙና ሊያድጉ የሚችሉ ናቸው ተብሏል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፓትሪሺያ ስፒኖዛ ተሸላሚዎቹ ከማህበረሰብ መሪዎች፣ አረንጓዴ ልማት ላይ ከተሰማሩ ተቋማትና መንግስታት የተውጣጡ ናቸው ብለዋል፡፡
ሊያድጉና ሊሰፉ የሚችሉት እነዚህ ፕሮጄክቶች የአየር ንብረት ለውጥን የመዋጋቱን ሂደት በመደገፍ ረገድ ትልቅ አበርክቶ ሊኖራቸው እንደሚችልም ነው ስፒኖዛ የተናገሩት፡፡
ላለፉት 11 ቀናት ሲካሄድ የቆየው የመንግስታቱ ድርጅት 25ኛ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ነገ ታህሳስ 03 ቀን 2012 ዓ.ም. ይጠናቀቃል፡፡ ከመላው ዓለም የተውጣጡ 27ሺ ገደማ ባለስልጣናት፣ ባለሙያዎች፣ ባለሃብቶች እና ጋዜጠኞች በጉባዔው በመታደም ላይ ናቸው፡፡
መረጃው ከተባበሩት መንግስታት ይፋዊ ድረ-ገጽ የተገኘ ነው፡፡