ይህን ለማድረግ የሚያስችል ምክክር ከሰሞኑ ይካሄዳል ተብሏል
ከሳምንት በፊት በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር ጊኒ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት የመሩት ሌተናል ኮሎኔል ማማዲ ዱምቦያ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ጠየቁ፡፡
ኮሎኔል ማማዲ ሁሉን ያካተተ የሲቪል መንግስት እንዲቋቋም ጠይቀዋል፡፡
በዚህም የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ምሁራን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች የተካተቱበት የምክክር መድረክ በዚህ ሳምንት ይካሄዳል ተብሏል፡፡
ምክክሩ ለአራት ቀናት የሚካሄድ ነው እንደ ፍራንስ 24 ዘገባ፡፡
ኮሎኔል ማማዱ እና ጓዶቻቸውን ኮናክሪ በሚገኘው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው በጊዜያዊነት ተጠልለው ያሉት፡፡
ከስልጣን የተወገዱት የቀድሞው ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴም በዚያው ታስረው ይገኛሉ፡፡ ታዲያ ምክክሩ በዚሁ በፓርላማው ቅጥረ ግቢ እንደሚካሄድ ነው የተነገረው፡፡
የአልፋ ኮንዴን በኃይል ከስልጣን መነሳት ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት እንዲሁም የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ጊኒን ከአባልነት ማገዱ የሚታወስ ነው፡፡