ስምምነቱ እስራኤል አንዳንድ የፍልስጤም ግዛቶችን ወደ ራሷ ለማካተት የያዘችውን ዕቅድ እንድታቋርጥ ለማድረግ የሚያስችል ነው
ዩኤኢ እና እስራኤል ታሪካዊ ከተባለ ስምምነት ደረሱ
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና እስራኤል ታሪካዊ ካሉት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታወቁ፡፡
ስምምነቱ እስራኤል አንዳንድ የፍልስጤም ግዛቶችን ወደ ራሷ ለማካተት የጀመረችውን ጥረት እንድታቋርጥና ከዩኤኢ ጋር ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን እንድትመሰርት ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡
የአቡዳቢ ልዑል አልጋወራሽ እና የዩኤኢ ጦር ኃይሎች ምክትል የበላይ አዛዥ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ባደረጉት ውይይት ነው ስምምነት ላይ የተደረሰው፡፡
በስልክ ባወራንበት ወቅት እስራኤል አንዳንድ የፍልስጤም ግዛቶችን ወደ ራሷ ለማካተት የጀመረችውን ጥረት እንድታቋርጥ ተስማምተናል ያሉት ልዑል አልጋወራሹ ለመተባበርና የሁለትዮሽ ግንኙነት ለመመስረት የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት ስምምነት ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ትልቅ እመርታ ሲሉ ታሪካዊ ያሉትን ስምምነት ገልጸውታል፡፡
በሶስቱ ሃገራት የጋራ መግለጫ ለመካከለኛው ምስራቅ ደህንነት ያላትን ቁርጠኝነት የገለጸችው አሜሪካ ከዩኤኢ ጋር ያላትን ወታደራዊ ትብብር እንደምታጠናክር አስታውቃለች፡፡
የሁለቱ ሃገራት ባለስልጣናት በመጪዎቹ ሳምንታት ተገናኝተው ስምምነቱን እንደሚፈርሙም በመግለጫው ይፋ ሆኗል፡፡
ስምምነቱ በሃገራቱ መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት፣የቱሪዝም፣የአየር በረራ፣የደህንነት እና የሌሎች ዘርፎች ግንኙነት ለማጠናክ የሚያስችል ነው ዋም እንደተሰኘው የዩኤኢ ዜና አገልግሎት ገለጻ፡፡
ኤምባሲዎቻቸውን በመክፈትም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከርም ያስችላል፡፡
አስራኤል የጀመረችውን የፍልስጤም ግዛቶችን የማካተት እርምጃ አቋርጣ ከሌሎች ሙስሊም የአረብ ሃገራት ጋር ያላትን ግንኙነት እና ትብብር ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮችም ላይ ትኩረት አድርጋ ትሰራለች፡፡
የሃገራቱ ግንኙነት መሻሻል ለአሜሪካ የቀረበ ወዳጅነት ያላቸውን ሁለቱን ሃገራት ይበልጥ እንዲቀራረቡ ለማድረግ እና ስትራቴጂክ ዋጋ አላቸው የሚባልላቸውን የቀጣናውን የዲፕሎማሲ፣የንግድ እና የደህንነት አጀንዳዎች በትብብር ለማስተግበርም ያግዛል፡፡
ዩኤኢ ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል ስምምነትን የፈረመች ሶስተኛዋ የመካከለኛው ምስራቅ ሃገር ነች፡፡
ከአሁን ቀደም ግብጽ እ.ኤ.አ በ1979 ዮርዳኖስ እ.ኤ.አ በ1994 ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያጠናክር የሁለትዮሽ ስምምነት መፈረማቸው የሚታወስ ነው፡፡