የዩኤኢ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአቡ ዳቢ የሚገኘውን የኢራን ኤምባሲ ወኪል አምባሳደር ለማብራሪያ ጠራ
የእስራኤል እና የዩኤኢ የሰላም ስምምነት ዩኤኢን እና ኢራንን አፋጧል
ዩኤኢ ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ለማደስ መስማማቷን ተከትሎ ኢራን የምትሰነዝረውን ዛቻ አጥብቃ ተቃውማለች
የዩኤኢ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአቡ ዳቢ የሚገኘውን የኢራን ኤምባሲ ወኪል አምባሳደር ጠርቶ ማብራሪያ ጠየቀ
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ዛሬ በሀገሪቱ መዲና አቡ ዳቢ የሚገኘውን የኢራን ኢስላማዊ ሪፓብሊክ ኤምባሲ ወኪል አምባሳደር ወደ ሚኒስቴሩ ዋና ጽ / ቤት ጠርቶ አነጋግሯል። የኢራን ባለስልጣናት በዩኤኢ ላይ የሚሰነዝሩትን የዛቻ ንግግር በተመለከተ በውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር የፖለቲካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር አምባሳደር ካሊፋ ሻሂን ካሊፋ አል ማራር ናቸው ወኪል አምባሳደሩን በጽ/ቤታቸው ያነጋገሩት።
የኢራን ፕሬዝዳንት ሀሰን ሩሀኒ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ከእስራኤል ጋር መደበኛ ግንኙነት ለመጀመር መስማማቷን በማስመልከት ባደረጉበት ንግግር በዩኤኢ ላይ መዛታቸውን በመቃወም ነው ወኪል አምባሳደሩን ማብራሪያ የጠየቁት።
ከፕሬዝዳንት ሩሀኒ በተጨማሪ የዩኤኢን ሉዓላዊ ውሳኔ በተመለከተ ከኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ ከአብዮታዊ ጥበቃ እና ከሌሎችም የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተደጋጋሚ ዛቻዎች እየተሰነዘሩ መሆኑንም አምባሳደር ካሊፋ አንስተዋል።
የዩኤኢ ውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ረዳት ሚኒስትሩ አምባሳደር ካሊፋ አል ማራን የኢራን ባለስልጣናትን የዛቻ ንግግሮች በመተቸት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠንካራ የተቃውሞ መግለጫ ለወኪል አምባሳደሩ በጽሑፍ ሰጥተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ይህ የኢራን ንግግር ተቀባይነት የሌለው ነው የሚል አቋም ያለው ሲሆን በአረብ ባሕረ ሰላጤ አካባቢ ደህንነት እና መረጋጋት ላይ ከፍተኛ ስንክሳር ያስከትላል ሲሉ ረዳት ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
የባለስልጣናቱን የዛቻ ንግግር እና ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ በሚገኙ የውጭ የዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን መነሻ በማድረግ ፣ ኢራን በቪየና የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ስምምነት መሠረት በሀገሪቱ ለሚገኙ የዩኤኢ ሚሲዮኖች እና ዲፕሎማቶች አስፈላጊውን ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባትም አሳስበዋል።
በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና በእስራኤል መንግስታት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የኢራን ባለስልጣናትን ፀብ አጫሪ ንግግሮች ዩኤኢ ሙሉ በሙሉ እንደማትቀበል ረዳት ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡ ይህ የኢራን በውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ የመግባት እና ሉዓላዊነትን መዳፈር የሀገራትን ግንኙነት የሚገዛውን የዓለም አቀፍ ህግ መርሆዎች የሚፃረር መሆኑን በአጽንኦት አንስተዋል፡፡ ለቀጣናው መረጋጋት የማይጠቅሙ የኢራን መግለጫዎችንም ዩኤኢ እንደማትቀበል አምባሳደር ካሊፋ አል ማራን የገለጹ ሲሆን በሀገሮች መካከል የሚደረጉ ግንኙነቶች ፣ ስምምነቶች እና ፊርማዎች ሉዓላዊ ጉዳይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
ዩኤኢ ከእስራኤል ጋር የደረሰችውን ስምምነት የተቃወሙት የኢራን ፕሬዚዳንት ሀሰን ርሀኒ ባደረጉት ንግግር "ዩኤኢ ትልቅ ስህተት ሰርታለች" ያሉ ሲሆን "በቀጣናው እስራኤል እንድትገባ በር በመክፈት ክህደት ፈጽማለች" በማለት ዩኤኢ ስምምነቱን እንድታፈርስ አሳስበዋል።