“የኢትዮጵያ ጉብኝቴ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደሰትኩበትና የተጠቀምኩበት ነበረ”-ሞሃመድ ሃምዳን ደገሎ
“ስለዚህ በኢኮኖሚው ዘርፍ ያሉ የካርቱም ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ሄደው ያለውን ተጨባጭ ለውጥ ማየት አለባቸው”
“ኢትዮጵያ ትክክለኛውን የልማት አቅጣጫ የያዘች ሃገር እንደሆነች በጉብኝቴ ተመልክቻለሁ”
“የኢትዮጵያ ጉብኝቴ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደሰትኩበትና የተጠቀምኩበት ነበረ”
በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የተለየ እና ብዙ ቁም ነገሮችን የቀሰሙበት እንደነበረ የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ሃምዳን ደገሎ (ሄሜቲ) ተናገሩ፡፡
ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጉብኝታቸውን አስመልከተው በካርቱም ጋዜጣዊ መግለጫን ሰጥተዋል፡፡
ለተደረገላቸው አቀባበል ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድን ያመሰገኑት ደገሎ በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ አመርቂ ውይይቶችን ማድረጋቸውንና የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ የድንበር ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች፣ በሱዳንና ደቡብ ሱዳን፣ በአቢዬ ግዛት ችግሮች እንዲሁም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተናል ያሉም ሲሆን በጉዳዮቹ ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ነው የገለጹት፡፡
ወደፊት በእነዚህና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ የሚያጋጥም ችግር ካለ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆኗቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸውልኛል ብለዋል ሞሃመድ ሃምዳን ደገሎ፡፡
ይህ የተለያዩ የልማት ፕሮጄክቶችን ስንጎበኝ የነበረ በመሆኑ ምክንያት ለሁለት ቀናት የነበረውን ጉብኝት ለሶስት ቀናት አራዝመናል ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ “ለመጀመሪያ ጊዜ የተደሰትኩበትና የተጠቀምኩበት” ሲሉ ነው ስለ ጉብኝታቸው የሚያስቀምጡት፡፡
ትልቅ ትምህርት አግኝተንበታል ያሉም ሲሆን “ኢትዮጵያ ትክክለኛውን የልማት አቅጣጫ የያዘች ሃገር እንደሆነች የገነባቻቸውን ትላልቅ መሰረተ ልማቶች በጎበኘሁበት ወቅት ተመልክቻለሁ” ሲሉ አስቀምጠዋል፡፡
“በዚህ ጉብኝት የተሰማኝ ልክ የሌለው ደስታ ነው፤ ከዚህ በፊት ያላየሁትን ነው ያየሁት፤ ጉብኝታችን በእኛ በኩል ያሰብናቸውን ብዙ ነገሮች አቅሎልናል”ም ብለዋል፡፡
“ስለዚህ በኢኮኖሚው ዘርፍ ያሉ የካርቱም ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ሄደው ያለውን ተጨባጭ ለውጥ ማየት አለባቸው” ሲሉም ነው ደገሎ የገለጹት፡፡
በቆይታቸው የተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ የመንገድና ሌሎችንም በአራት ኪሎ ቤተመንግስት አቅራቢያ የሚሰሩ እና የሸገርን ማስዋብ አካል የሆኑ የልማት ስራዎችን እንዲሁም የእንጦጦ ፓርክን ጎብኝተዋል፡፡ አይቲ ፓርክን ጨምሮ የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መሰረተ ልማትንም ተመልክተዋል፡፡
“ዐቢይ አስተከላቸው ስለሚባሉ 5 ቢሊዬን ችግኞች አትደነቁ” ሲሉ የሚናገሩት ደገሎ “በችግኝ ማፍያ ቦታዎች ከዚህም በላይ እስከ 20 ቢሊዬን ችግኞችን ለመትከል የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ በአይኔ የተመለከትኩት” ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ እንደጀመረች የተመለከትናቸው ስራዎች ሁሉ እንዲሳኩላት እንመኛለን ሲሉም ነው መልካም ምኞታቸውን የገለጹት፡፡
ሁለቱን ሃገራት በባቡር መሰረተ ልማት ለማገናኘት ስለተጀመረው ስራ ተወያይተናል ያሉም ሲሆን የራሳችንን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
ደገሎ “ከኢትዮጵያ ጋር ብዙ የሚያስተሳስሩን ብዙ ነገሮች አሉ”ም ነው ያሉት፡፡
ወጣቶች ልምድ እና ተሞክሮ ይቀስሙ ዘንድ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልኩም ነው የተናገሩት፡፡ በቅርብ ጊዜ ባለሙያዎቻችንን ሰብሰብ አድርገን ስለ ጎበኝናቸው ነገሮች እንወያያለንም ብለዋል፡፡