በደቡብ ሱዳን እየታየ ያለው ነገር “በጣም አደገኛ እና የሰላም ስምምነቱን የሚያፈርስ” ነው - ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)
ዋና ጸሃፊው “በመስቀለኛ መንገድ ላይ” የምትገኝ ሀገር ናት ሲሉም ስለ ሶማሊያ ተናግረዋል
ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር የተፈጠረውን ችግር የማስቆም “የህግም ሆነ የሞራል ግዴታ አለባቸው”ም ብለዋል የኢጋድ ዋና ጸሃፊው
ሰሞኑን በደቡብ ሱዳን እየታየ ያለው ነገር “በጣም አደገኛ” ነው ሲሉ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስት (ኢጋድ) ዋና ጸሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት ዶ/ር ወርቅነህ “በጣም አደገኛ” ያሉት ነገር ከጥቂት አመታት በፊት በአዲስ አበባ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት የሚያፈርስ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ዋና ጸሃፊው በቆይታቸው ከደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ወቅታዊ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታዎች ጋር የተያያዙ ማብራሪያዎችን ለአል ዐይን ሰጥተዋል፡፡
እንደ ሃገር ከተመሰረትች ከ12 ያልበለጡ ዓመታትን ያስቆጠረችው ከአፍሪካ አህጉር 55ኛዋ ሀገር ደቡብ ሱዳን ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ምናልባትም በዓለም ላይ ብቸኛ የሆነና አራት ምክትል ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም ከ1 ሺ በላይ እንደራሴዎች ያካተተ ግዙፍ መንግስት ለመመስረት ችላለች፡፡ ይህም እንደ ትልቅ ስኬት ይነሳል፡፡ ሆኖም በአስራዎቹ እድሜ ላይ የምትገኘው ሃገር አሁንም ድረስ ፈተናዎች እንደበዙባት ናት፡፡
በተለይ በዚህ ሳምንት በሀገሪቱ እየታየ ያለው ምልክት በጣም አደገኛና ሀገሪቱን ዳግም ወደ ትርምስ እንዳያስገባት ተሰግቷል፡፡ ወትሮም ቢሆን ተቀናቃኝ የነበሩት ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ምክትላቸው የነበሩት ሬይክ ማቻር ዳግም መቃቃር መጀመራቸው እጅግ አደገኛ እንደሆነም በርካታ የፖለቲካ ልሂቃን ሲናገሩ ይደመጣል፡፡
የሃገሪቱ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች በፈረንጆቹ 2018 አንድ ቁልፍ ስምምነትን አድርገው ነበረ፡፡ ስምምነቱም አንድ ወጥ የሆነ ብሔራዊ ጦርን እናቋቁም የሚል ነበር፡፡ የፖለቲካ ኃይሎቹ በሁለተኛ ምዕራፍነት በተጠቀሰው በዚህ ስምምነት መግባባት ላይ መድረስ ይጠበቅባቸውም ነበር፡፡ ሆኖም ብሔራዊ ጦሩን በማዋቀሩ ሂደት ምን ያህል ኃይዋጣ፣ የስልጣን ክፍፍሉ ምን ይምሰል እና ስብጥሩስ በሚሉ ጉዳዮች ላይ አልተስማሙም፡፡
በዚህም የደቡብ ሱዳን ጉዳይ አሁንም ገና ነው እንደ ኢጋድ ዋና ጸሃፊው ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ገለጻ፡፡ እየታየ ያለው ምልክት “እጅግ አደገኛና የሰላም ስምምነቱን የሚያፈርስ ነው” የሚሉት ዋና ጸሃፊው፤ ስምምነቱ ከፈረሰ ደግሞ “ወደ እርስ በርስ ጦርነት ተገባ ማለት ነው” ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
በሀገሪቱ ያለውን ሁኔታን በተመለከተ ለሁሉም የኢጋድ አባል ሀገራት መሪዎች በመደወል እንዲያውቁት አድርጊያለሁ የሚሉት ዶ/ር ወርቅነህ፤ የሀገሪቱ መሪዎች ታሪካዊ ሃላፊነተቸው ሊወጡ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር የተፈጠረውን ችግር የማስቆም “የህግም ሆነ የሞራል ግዴታ አለባቸው”ም ነው ዶ/ር ወርቅነህ የሚሉት፡፡ ሌሎቹ ፖለቲከኞች የህዝባቸው ሰቆቃ እንዲያበቃ በኃላፊነት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በኢጋድ በኩል የተፈጠረውን ቀውስ ባለበት እንዲቆም ጥረት እየተደረገ መሆኑንና በአሁኑ ወቅት የኢጋድ ልዩ መልእክተኛ ጁባ እንደሚገኙም ነው የገለጹት፡፡
የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ አስጊ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ዋና ጸሃፊው “እኔም በቀጣይ ወደ ደቡብ ሱዳን እሄዳለሁ፤ የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ እንጥራለን” ብለዋል፡፡
ለሁለት አስር ዓመታት ያህል መንግስት አልባ ሆና የቆየችው ሶማሊያም እጅግ ፈታኝ በሆነ ወቅት ላይ ትገኛለች፡፡ በርካታ ፈታናዎችን ተሻግራ ምርጫን አጀንዳ ወደ ለማድረግ ብትበቃም ከምርጫው መራዘምና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቷ አልቀረም፡፡
ዶ/ር ወርቅነህም ሶማሊያ “በመስቀለኛ መንገድ ላይ የምትገኝ ሀገር” ሲሉ ይገልጿታል፡፡
ሶማሊያውያን ከወራት በኋላ የሚያካሂዱትና በተወካዮቻቸው አማካኝነት መሪያቸውን የሚመርጡበት ምርጫ፤ የሀገሪቱን የወደፊት እጣፈንታ የሚወስን ቁልፍ ምዕራፍ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
እስካሁን ድረስ ያለው የምርጫ ሂደት የሚበረታታ ነው ያሉት ዋና ጸሃፊው ሶማሊያውያን ምርጫውን ተዓማኒ፣ ግልጽ እና ፍትሃዊ እንዲሆን በማድረግ የሀገሪቱን ቀጣይ ጉዞ የተሳካ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡
ጠንካራ ሶማሊያን እውን ማድረግ “የቀጠናው ስጋት የሆነውን አልሻባብ” ለመዋጋት ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ጭምር ነው ዶ/ር ወርቅነህ የተናገሩት፡፡
“አልሻባብ ቢዳከምም ጨርሶ አልጠፋም” የሚሉት ዋና ጸሃፊው፤ ኢጋድ የአባል ሀገራቱን የጸጥታ ተቋማት ለማጠናከር በጥናት ላይ የተመረኮዙ ድጋፎች እያደረገ ነውም ብለዋል፡፡
ከፈረንጆቹ ጥቅምት 25 ወዲህ በከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ የምትገኘው የሌላኛዋ ጎረቤት ሃገር ሱዳን ጉዳይም እንዲሁም ኢጋድን ከሚመለከቱ ቀዳሚ ቀጣናዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ሱዳን የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር ነች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሯም መቀመጫውን ጂቡቲ ያደረገውን ተቋም በሊቀመንበርነት ይመራሉ፡፡ ሆኖም ይህ መሆኑ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ተጠቃሽ አላደረጋትም፡፡
ዶ/ር ወርቅነህም በሱዳን ያለውን ሁኔታና ወቅታዊ ችግር ለማወቅ የኢጋድ ልዑክ ተልኮ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
“እንደ ኢጋድ ከተመድ እና አፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር በሱዳን ፖለቲከኞች መካካል ያለውን ልዩነት ለማሸማገል እየሰራን ነው” ሲሉም ነው ዋና ጸሃፊው ያስቀመጡት፡፡
ኢጋድ በተለያዩ መስኮች ያለውን ቀጣናዊ ትብብር እና መደጋገፍ ለማሳደግ በማሰብ ነበር ከ35 ዓመታት በፊት የተቋቋመው፡፡ ከዚያም ወዲህ የቀጠናውን ችግሮች ከመፍታት አንጻር በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፤ ቀጣናዊ ምጣኔ ሃብታዊ ትስስርን በማቀላጠፍ ውህደትን ለማምጣት በመስራትም ላይ ይገኛል፡፡ ሆኖም በጥንካሬው ይተቻል፡፡ የአባል ሃገራቱን ችግሮች በመፍታትና ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን ረገድ ውስንነቶች እንዳሉበትም ይጠቀሳል፡፡
ተቋማቸው ለበርካታ ችግሮች ተጋላጭ በሆነው በዚህ ቀጠና አሳካሁ የሚለው ነገር እንዳለ የተጠየቁት ዶ/ር ወርቅነህ “አዎ፤ አዝጋሚ ቢሆኑም በርካታ ስኬች ተመዝግበዋል፤ ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል በጦርነት ምክንያት መንግስት አልባ ሆና የቆየችው ሶማሊያ አዲስ መንግስት እንድትመሰርት፣ በደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት እንዲደረስ ከፍተኛውን ሚና ሲጫወት የነበረው ኢጋድ ነው፤ እነዚህ በስኬት ሊነሱ የሚችሉ ናቸው” ሲሉ መልሰዋል፡፡
በየሀገራቱ የሚፈጠሩ ችግሮች የመፍታቱ ሃላፊነት በዋናነት የመሪዎቹና የህዝቦቹ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው የሚናገሩት ዶ/ር ወርቅነህ፤ በአባል ሀገራቱ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቅረፍና ሰላም ለማምጣት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢጋድ ከፍተኛ ሚና ሲጫወት መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡