“አደገኛ ነው” ከተባለ መቃቃር ውስጥ ገብተው የነበሩት የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች ተስማሙ
ስምምነቱ ለመገንባት በታሰበው ብሔራዊ ጦር ወጥነት ያለው እዝን ለመፍጠርና ስልጣን ለመከፋፈል የሚያስችል ነው ተብሏል
ተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎቹ ችግራቸውን ለመፍታ የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል
ከሰሞኑ አደገኛ ነው ከተባለ መቃቃር ውስጥ የነበሩት የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ኃይሎች ተስማሙ፡፡
የፖለቲካ ኃይሎቹ በሱዳን ሸምጋይነት ነው የተካረረ መቃቃር ውስጥ የከተታቸውን ችግር ለመፍታት በዋና ከተማቸው ጁባ የተስማሙት፡፡
ስምምነቱ ከሁሉም የተውጣጣና ጠንካራ ብሔራዊ ጦርን ለመመስረት የሚያስችል ነው፡፡ ይህን ለማጽናት የሚያስችል ሰነድ ተዘጋጅቶም ተፈራርመዋል፡፡
ፊርማው የፓለቲካ ኃይሎቹን የማሸማገሉን ሚና በወሰዱት የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ጄ/ል መሃመድ ሃምዳን ደገሎ በተገኙበት የተፈረመ ነው፡፡
ለመገንባት በታሰበው ብሔራዊ ጦር ወጥነት ያለው እዝን ለመፍጠርና ስልጣን ለመከፋፈል እንደሚያስችልም ተነግሮለታል፡፡
በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና በምክትላቸው ሬይክ ማቻር (ዶ/ር) በሚመሩ ኃይሎች መካከል የተፈጠረውን መቃቃር በማርገብ ለማስማማት ያደረግነው ጥረት ተሳክቶልናል ያሉት ጄ/ል መሃመድ ሃምዳን ደገሎ ወንድሞቻችን የሃገራቸውን ሰላምና ደህንነት ለማስቀጠል በሚያስችል ትክክለኛ መንገድ ላይ በመገኘታቸው ደስተኞች ነን ሲሉ መሪዎቹን አመስግነዋል፡፡
ከነጻነት በኋላ ዓመታትን በእርስበርስ ጦርነት ያሳለፉት በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና በሬይክ ማቻር የሚመሩ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ኃይሎች ከጥቂት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ የፈረሙትን የሰላም ስምምነት ሊያፈርስ ከሚችል መቃቃር ውስጥ ገብተው ነበር፡፡
መቃቃሩ በስምምነቱ መሰረት ሊዋቀር ከታሰበው ብሔራዊ ጦር አመሰራረት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በስምምነቱ አተገባበር ላይ የነበራቸው የአካሄድ ልዩነት ሃገሪቱን ዳግም ወደ ጦርነት እንዳይከታት ተሰግቶ ነበር፡፡
እየታየ ያለው ነገር “በጣም አደገኛ ነው” ሲሉ ለአል ዐይን አማርኛ የተናገሩት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ዋና ጸሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በቶሎ ካልተፈታ የሰላም ስምምነቱን የሚያፈርስ እንደሆነ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡
ለደቡብ ሱዳን መረጋጋት ጉልህ ሚና ስታደርግ መቆየቷን የገለጸችው ኢትዮጵያ ከሰሞኑ በመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) የተመራና ምክትል የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙን ጄ/ል አበባው ታደሰን እንዲሁም የደህንነት ሚኒስትሩን ተመስገን ጥሩነህን ያካተተ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ወደ ጁባ መላኳ ይታወሳል፡፡