በፈረንሳይ ጭብል ያጠለቁ ታጣቂዎች "ዘ ፍላይ" የተባለውን የእጽ አዘዋዋሪ ለማስለቀቅ በፈጸሙት የደፈጣ ጥቃት ሁለት የእስርቤት ጠባቂዎችን ገደሉ
በፈረንሳይ የእጽ አዘዋዋሪን ለማስለቀቅ ጥቃት የከፈቱ ታጣቂዎች ሁለት ጠባቂዎችን ገደሉ።
በሰሜን ፈረንሳይ ጭብል ያጠለቁ ታጣቂዎች "ዘ ፍላይ" የተባለውን የእጽ አዘዋዋሪ ለማስለቀቅ በእስረኛ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ በፈጸሙት የደፈጣ ጥቃት ሁለት የእስርቤት ጠባቂዎች የገደሉ ሲሆን ሌሎች ሶስት ሰዎችን ደግሞ አቁስለዋል።
በጥቃቱ ያመለጠውን ወንጀለኛ ለመያዝ ፓሊስ እያደነ ይገኛል።
በሰሜናዊ ፈረንሳይ በኡሬ ግዛት የተፈጸመው ጥቃት በመላው አውሮፓ የእጽ ወንጀል መስፋፋቱን የሚያመለክት ነው ተብሏል።
ጥቃቱ የተፈፈመው የፈረንሳይ ሴኔት የእጽ ዝውውር ሪፓርት ይፋ ባደረገበት እና በእጽ አማካኝነት የሚፈጸም ወንጀል በሀገሪቱ መሰረታዊ ጥቅሞች ላይ ስጋት ተደቅኗል ሲል ባስጠነቀቀበት ቀን ነው።
የፓሪስ አቃቤ ህግ እና ፖሊስ እንደገለጸው ከእስር ያመለጠው የ30 አመት የእጽ አዘዋዋሪ ሞሀመድ አምራ ይባላል። አምራ በወንጀል ተከተሶ በኢቨሩክስ በሚገኝ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ጥፋተኛ ተብሎ በቫል ዲ ሪዩል እስርቤት እንዲታሰር ተደርጎ ነበር።
አምራ ለሞት ባበቃ የእገታ ተግባር ተጠርጥሮ በማርሴሌ በሚገኝ አቃቤህግ ክስ ተመስርቶበት እንደነበር የፓሪስ አቃቤ ህግ ጠቅሷል።
የማርሴሌ የፖሊስ ምንጮች እንደሚገልጹት ከሆነ አምራ "ብላክስ" ከሚባል የጋንግ ቡድን ጋር ግንኙነት ያለው የእጽ አዘዋዋሪ ነበር።
በማህበራዊ ሚዲያ የተለቀቁ ምስሎች ጭምብል ያጠለቁ ታጣቂዎች በእሳት የተያያዘች ኤስዩቪ መኪናን ከበው ታይተዋል።
ኤስዩቪ በእስርቤት ተሽከርካሪዋ ላይ በፊት በኩል ግጭት በማድረስ ጉዳት ያደረሰች ይመስላል።
የአምራ ጠበቃ ሁጎስ ቪጀር በበኩሉ ግን አምራን ባለፈው እሁድ የታሰረበትን ክፍል የብረት መስኮት በመቁረጥ ለማምለጥ ሞክሮ እንደነበር ተናግሯል።
ቪጀር ይህ ለማምለጥ ዝግጅት መኖሩን የሚያሳይ ነው ብሏል።
የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ጀራልድ ዳርማኒን በመቶዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች የተሳተፉበት ፍላጋ እየተካሄደ ነው ብለዋል።
የፍትህ ሚኒስትሩ ኢሪክ ዱፖንድ ሞሪቲ የእስርቤቷ ተሽከርካሪ ወይም ቫን ጥቃት የደረሰባት አምራ ከምርመራ ዳኛው ጋር እንዲገናኝ ወደ ሮይን እየተወሰደ በነበረበት ወቅት መሆኑን ተናግረዋል።