የታጠቀ ግለሰብ በሊባኖስ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ተኩስ ከፈተ
የሶሪያ ዜግነት ያለው ግለሰብ ለግማሽ ስአት ከሊባኖስ ወታደሮችና ከኤምባሲው የጸጥታ ሃይሎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ማድረጉ ተገልጿል
በ1983 በቤሩት በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከ60 በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል
በሊባኖስ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ ዛሬ ጠዋት ጥቃት የማድረስ ሙከራ ተደርጓል።
የሶሪያ ዜግነት አለው የተባለ የታጠቀ ግለሰብ ከኤምባሲው እና ከሊባኖስ የጸጥታ ሃይሎች ጋር ለግማሽ ስአት ያህል የተኩስ ልውውጥ ማድረጉንም ነው የሊባኖስ ጦር ያስታወቀው።
የሊባኖስ ወታደሮች ጥቃት አድራሹ ግለሰብ ላይ ተኩሰው ጉዳት አድርሰውበት ወደ ሆስፒታል መወሰዱ ተገልጿል።
የአሜሪካ ኤምባሲ በበሩ ዙሪያ በተካሄደው የተኩስ ልውውጥ በሰራተኞቹ ላይ ጉዳት እንዳልደረሰ መግለጹን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ሬውተርስ በበኩሉ አንድ የኤምባሲው የደህንነት ቡድን አባል በጥቃቱ መቁሰሉን ምንጮቹን ጠቅሶ አስነብቧል።
የሊባኖስ ጦር በኤምባሲው ዙሪያ ወታደሮችን በማሰማራት ተጨማሪ ጥቃት አድራሾች ካሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል አሰሳ እያደረገ መሆኑን ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
ከቤሩት በስተደቡብ ኡካር በተባለ ስፍራ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በርካታ የፍተሻ ጣቢያዎች ያሉትና ደህንነቱ አስተማማኝ እንደነበር ሲነገርለት ቆይቷል።
ዋሽንግተን በቤሩት የሚገኘውን ኤምባሲዋን ወደ ኡካር ያዛወረችው በፈረንጆቹ 1983 በኤምባሲው በተፈጸመ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት 63 ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነበር።
በ1984ም ወደ ኡካር በተዛወረው ኤምባሲ ላይ የቦምብ ጥቃት መፈጸሙን አሶሼትድ ፕረስ አስታውሷል።
ለ1983ቱ ጥቃት የሊባኖሱን ሄዝብላህ ተጠያቂ ያደረገችው ዋሽንግተን ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ያላት ድርሻ በሊባኖሳውያን ተቃውሞ አስነስቶባታል።
የጋዛው ጦርነት እንደተጀመረ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሊባኖሳውያን በአሜሪካ ኤምባሲ ዙሪያ በመገኘት ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ከሊባኖስ የጸጥታ ሃይሎች ጋር መጋጨታቸው ይታወሳል።