አሜሪካ ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ የጸጥታው ምክር ቤት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠየቀች
ዋሽንግተን በሁለቱ ተዋጊዎች መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረግ ያቀረበችው ሀሳብ ተቀባይነት እንዲኖረው ነው የምክር ቤቱን ድጋፍ የጠየቀችው
አሜሪካ ለሀማስ እና እስራኤል በላከችው ሰነድ የተኩስ አቁሙ ለ6 ሳምንታት እንዲቆይ ጠይቃለች
አሜሪካ በእስራኤል እና በሀማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቃለች።
ለጋዛው ጦርነት ዘላቂ መፍትሄን ለማበጀት ያግዛል በሚል በአሜሪካ የተዘጋጀው የተኩስ አቁም ጥያቄ ረቂቅ ሰነድ በተባበበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንዲደገፍ ዋሽንግተን ጠይቃለች፡፡
ለተኩስ አቁም ስምምነት ሀሳቡ ተቀባይነት ተፈጻሚነት እና ስኬታማነት የምክር ቤቱ ድጋፍ ያሻኛል ያለችው ሀገሪቱ በቀጣይ ሁለቱ ወገኖች ወደ ተኩስ አቁም በሂደትም ወደ ጦርነት ማቆም ይመጡ ዘንድ ተመድ ያግዘኝ ብላለች፡፡
አሜሪካ ያዘጋጀችው የተኩስ አቁም ስምምነት ረቂቅ ሰነድ ሁለቱ ወገኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ተኩስ አቁም እንንዲመጡ፣ እስራኤል በርካታ ዜጎች ከሚኖሩባቸው የጋዛ ክፍሎች ጦሯን እንድታስወጣ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ፣ ፍልስጤማዊያን ወደሰሜናዊ ጋዛ እንዲመለሱ እና የእርዳታ መስመሮች እንዲከፈቱ ሀማስ ደግሞ ታጋቾችን እንዲለቅ ይጠይቃል፡፡
በአሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነት ዙርያ ትላንት በኢንተርኔት ስብሰባ አካሂደው የነበሩት የግበጽ፣ጆርዳን፣ሳኡዲ አረብያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እና ኳታር የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች በጋራ ባወጡት መግለጫ ረቂቁን እንደሚደግፉ ነገርግን እስራኤል ከጋዛ ሰርጥ ሙሉ ለሙሉ መውጣት እንዳለባት እና የመልሶ ግንባታዎችም መጀመር እንዳለባቸው በመግለጫቸው ጠይቀዋል፡፡
የተኩስ አቁም ረቂቅ ሰነዱ ጊዜያዊ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ቅድሚያ ቢሰጥም ሁለቱ ወገኖች ዘላቂ ጦርነት ማቆም ስምምነቶች ላይ እንዲወያዩ ለማስቻል አላማ እንዳለው ቪኦኤ አስነብቧል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር ከሰሞኑ ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ረቂቅ ሰነዱ ለሀማስ እንደደረስው እና ቡድኑ ከዚህ ቀደም የተኩስ አቁም እንዲደረግ ሲጠይቅ ያነሳቸው ሀሳቦች በረቂቁ ላይ ተካተዋል ብለዋል፡፡
የእስራኤል መንግስት ቃል አቀባይ በበኩላቸው እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብላለለች እየተባለ የሚነገረው ሀሰት ነው ብለዋል፡፡ ተኩስ አቁሙ የሚደረገው ዜጎቻችንን ለማስመለስ እና ቀጣይ በሚኖሩ ግንኙነቶች ዙርያ ለመምከር ነው ብለዋል፡፡ በነዚህ ወሳኝ ነጥቦች ዙርያ ከተስማማን እስራኤል የተኩስ አቁም ጥሪውን ለመቀበል ዝግጁ ናት ነው ያሉት፡፡
እስራኤል እና ሀማስ የአሜሪካን የተኩስ አቁም ጥሪ መልካምነት ከመናገራቸው በዘለለ እስካሁን ጥሪውን በይፋ መቀበሉን የገለጸ አካል የለም።
የተመድ የሰበአዊ ጉዳዮች ማስተባበርያ ቢሮ መረጃ እንደሚጠቁመው በአሁኑ ወቅት አንድ ሚልየን የሚሻገሩ ተፈናቃዮች በራፋ ይገኛሉ፡፡ የጥቅምት ሰባቱን የሃማስ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ባደረሰችው የምድር እና አየር ላይ ጥቃት 36400 ንጹሀን ሲገደሉ ከሟቾቹ መካከል አብዛኞቹ ህጻናት እና ሴቶች እንደሆኑ ይነገራል