ከምርጫ የተሰረዙት የጋዳፊ ልጅ አቤቱታ በሚያቀርቡበት በፍርድ ቤት ላይ ጥቃት መፈፀሙ ተሰማ
የሳኢፍ አል ኢስላም ጠበቃ " ድርጊቱ ለምርጫ ሂደቱ እንቅፋት ነው" ነው ብለዋል
ሳኢፍ አል ኢስላም ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እጩነት መሰረዛቸው ሊቢያን ወደሌላ ቀውስ እንዳይወስዳት ተሰግቷል
ከሊቢያ ፐሬዚዳናታዊ እጩነት የተሰረዙት የጋዳፊ ልጅ አቤቱታ ለማቅረብ ፍረድ ቤት ከመቅረባቸው ሰዓታት በፊት በፍርድ ቤት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸሙን የሀገሪቱ መንግስት ገለፀ።
የቀድሞ የሊቢያ መሪ የሙአማር ጋዳፊ ልጅ ሳኢፍ አል ኢስላም ጋዳፊ ከሊቢያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዕጩነታቸው መሰረዛቸውን የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን በትናትናው እለት መግለጹ ይታወሳል።
የቀድሞው መሪ ልጅ ከዕጩነት የተሰረዙበት ምክንያት “በሕግ የሚያስጠቃቸው ጉዳይ ስላለ” ነውም ብሎ ነበር ኮሚሽኑ።
ይሁን እንጂ ሳኢፍ አል ኢስላም ጋዳፊ ጨምሮ ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እጩነት የተሰረዙት 25 ሰዎች በ48 ሰዓታት ውስጥ ይግባኝ መጠየቅ መብት እንዳላቸው ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በዛሬው እለት በደቡባዊ የሀገሪቱ ከፍል ሰብሃ ከተማ በሚገኘው የሊቢያ ፍርድ ቤት ላይ የተፈጸመው ጥቃት፤ የጋዳፊ ልጅ ይግባኝ ለመጠየቅ ይመጣሉ ከተባሉበት ከሰዓታት በፊት መፈጸሙም ተነግሯል።
በፍርድ ቤቱ ላይ የተፈፀመው ጥቃትም በርካቶችን ያስደነገጠ መሆኑን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል/ኤ.ኤፍ.ፒ/ ዘግቧል።
የሳኢፍ አል ኢስላም ጠበቃ ካሊድ አል-ዛይዲ የሊብያ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች እና የፍትህ ሚኒስቴር መስርያ ቤቶች በጉዳዩ ላይ ምርመራ እንዲያካሂዱ ጠይቋል።
ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከድረጊቱ በፊት የፍርድ ቤቱን ሰራተኞች በሙሉ “በጠመንጃ” ሲያስገዱዱና ሲያስፈራሩ እንደነበርም አስታውቋል።
ካሊድ አል-ዛይዲ በሊቢያ መገናኛ ብዙሃን ላይ በቀረበው ቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት " ድርጊቱ ለምርጫ ሂደቱ እንቅፋት ነው" ሲሉ ተናግሯል።
የሳኢፍ አል ኢስላምን ጉዳይ በተመለከተ ኮሚሽኑ የምርጫ ህጉ አንቀጾችን ጠቁሞ እጩ ተወዳዳሪ “በወረደ ወንጀል የተፈረደበት መሆን የለበትም” እና ንጹህ የወንጀል ሪከርድ ማቅረብ እንዳለበት ይደነግጋል።
የይግባኝ ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የመጨረሻ የእጩዎች ዝርዝር በታህሳስ መጀመሪያ ላይ ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ከወደ ምስራቅ ሊብያ የተገኙት ጠንካራው ካሊፋ ሃፍታር፣ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሀሚድ ዲቤባህ እና የቀድሞ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፋቲ ባሻጋ በሊብያ ምርጫ የሚጠበቁ እጩዎች ናቸው።
ሁለቱም ፕሬዚዳንታዊ እና የህግ አውጭ ምርጫዎች ለታህሳስ 24 ተይዘው የነበረ ቢሆንም፤ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ፓርላማው የድምጾቹን ቀናት በመከፋፈል የህግ አውጪ ምርጫዎችን እስከ ወርሃ ጥር ድረስ እንዲራዘም ማድረጉ አይዘነጋም።
በፈረንጆቹ ታህሳስ 24 ቀን 2021 ይካሄዳል ተብሎ ከሚጠበቀው ምርጫ በርካታ ዕጩዎች መሰረዛቸው ወደ ዴሞክራሲ ትጓዛለች ተብላ የምትጠበቀው ሊቢያን ወደሌላ ቀውስ እንዳይወስዳት ያሰጋል ተብሏል።
የሊቢያ ምርጫ ኮሚሽን 98 በመቶ የሚሆኑ እጩዎችን መመዝገቡን መግለጹ ይታወሳል።