ሰይፍ አል እስላም ጋዳፊ በቀጣይ ወር በሀገሪቱ በሚካሄደው ምርጫ እንደሚሳተፍ ተገልጿል
የቀድሞ የሊቢያ መሪ ሙዓማር ጋዳፊ ልጅ ሰይፍ አል እስላም ጋዳፊ በቀጣይ ወር በሀገሪቱ በሚካሄደው ምርጫ እንደሚሳተፍ ተገለጸ፡፡
የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽኑ ባለስልጣን እንደገለጹት ታህሳስ 24 ቀን በሊቢያ በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እጩ በመሆን ከተመዘገቡት መካከል የቀድሞ የሊቢያ መሪ ሙአማር ጋዳፊ ልጅ ሰይፍ አል እስላም ጋዳፊ አንዱ ነው፡፡
ሰይፍ አል እስላም ጋዳፊ ፕሬዝዳንታዊ እጩ ሆኖ መመዝገቡ አሁን ላይ መረጋገጡን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የ 49 ዓመቱ የጋዳፊ ልጅ ዛሬ በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው ሴብሃ ከተማ ለፕሬዝዳንትንት ለመወዳደር ዕጩ ሆኖ ሲፈርም ታይቷል ነው የተባለው፡፡
የሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል ጦር አዛዥ ካሊፋ ሃፍታር እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሃሚድ አል ዲቤይባህ እና የፓርላማ አፈ ጉባዔው አጉሊያ ሳሌህ ለምርጫው ከሚወዳደሩት መካከል እንደሚገኙበትም ተጠቅሷል፡፡
የሊቢያው የቀድሞ መሪ ሙአመር አል ጋዳፊ ልጅ ሰይፍ አል እስላም ጋዳፊ እ.ኤ.አ በ 2011 አባቱ በኔቶ መራሹ ተልዕኮ ከመገደላቸው በፊት ሁነኛ የሀገሪቱ ሰው እንደነበር ይገለጻል፡፡
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፤ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪዮ ድራጊ እና ሌሎች ዓለም አቀፋዊ እንዲሁም ቀጣናዊ ባለስልጣናት በተገኙበት ሊቢያን የተመለከተ ጉባዔ ተደርጓል፡፡
በዚህ ጉባዔም በቀጣዩ ወር በሊቢያ የሚካሄደውን ምርጫ የሚያደናቅፍ አካል ማዕቀብ እንደሚጣልበት ስምምነት ላይ መደረሱን ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡
የቀድሞ የሊቢያ መሪ ሙአማር ጋዳፊ ሁለተኛ ወንድ ልጅ ሰይፍ አል እስላም ጋዳፊ፤ በለንደን የኢኮኖሚክስ ትምህርት ተምሯል፡፡ ኒዉዮርክ ታይምስ እንደገለጸው የሰይፍ አል እስላም ጋዳፊ የምዕራብ ሀገራት ወዳጆች የሊቢያ አዳኝ እንደሆነ ይናገሩለታል፡፡
ሊቢያ እ.ኤ.አ ከ 2011 ጀምሮ በእርስ በእርስ ጦርነት እየታመሰች ሲሆን በፈረንጆቹ ታህሳስ 24 የሚካሄደው ምርጫ ግን ከ 10 ዓመት በኋላ ሀገሪቱን ወደ ሰላም ይመልሳል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ በኔቶ የተመራውና ሙአማር ጋዳፊን ከስልጣን ያስወገደው ተልዕኮ በበርካቶች እንደ ስህተት ሲወሰድ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባም ትልቅ ስህተት እንደነበር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የጋዳፊ ልጅ ሰይፍ አል እስላም ጋዳፊ ላለፉት 10 ዓመታት ከሊቢያ ሕዝብ ተሰውሮ መቆየቱን ከኒውዮርክ ታይምስ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ገልጾ ነበር፡፡