በኢኳዶር የታጠቁ ግለሰቦች የቴሌቪዥን ጣቢያን ሲቆጣጠሩ በቀጥታ ተላልፏል
የሀገሪቱ መንግስት 22 የወንበዴ ቡድን መሪዎችን በሽብርተኝነት መፈረጁን ተከትሎ አመጽ ተቀስቅሷል
በኢኳዶር በአመጽና ሁከት ምክንያት በ2023 ከ8 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል
በኢኳዶር ታጣቂዎች በቀጥታ ስርጭት ላይ የነበረ የቴሌቪዥን ጣቢያን ሰብረው በመግባት ጋዜጠኞችን አንበርክከው ሲያስፈራሩ በቀጥታ ተላልፏል።
ጥቁር ጭንብል ያደረጉት ታጣቂዎች ጉያኪዩል በተባለችው ከተማ የሚገኘውን ቲሲ የተሰኘ የቴሌቪዥን ጣቢያን ነው ለመቆጣጠር ሙከራ ያደረጉት።
የቴሌቪዥን ጣቢያው ሰራተኞች በታጣቂዎቹ የደረሰባቸው እንግልት በቀጥታ ለ20 ደቂቃዎች ከተላለፈ በኋላ ስርጭቱ መቋረጡ ተዘግቧል።
የኢኳዶር ፖሊስ የቲሲ ቴሌቪዥን ጣቢያን ሰብረው ከገቡት ውስጥ 13ቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ታግተው የነበሩት ሰራተኞች በሙሉ ተለቀው የቴሌቪዥን ጣቢያውም ወደ ስርጭት መመለሱን አስታውቋል።
ኢኳዶር በእጽ አዘዋዋሪዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ያወጀችው የ60 ቀናት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰኞ እለት መተግበር ከጀመረ ወዲህ አመጽ ተቀስቅሶባታል።
በህዳር ወር 2023 ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዝዳንት ዳኔል ኖቦአ 22 የወንበዴ ቡድን መሪዎችን በሽብርተኝነት መፈረጃቸውም በተለያዩ የእስርቤቶች አመጽ እንዲነሳና እስረኞችን የማስመለጥ እንቅስቃሴ በስፋት እንዲካሄድ ማድረጉን ነው ሬውተርስ የዘገበው።
ፕሬዝዳንቱ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት አዲስ ማረሚያ ቤት ለመገንባትና የወንበዴ ቡድን መሪዎችንም ወደዚሁ ማረሚያ ቤት ለማዘዋወር ማቀዳቸውም የሁከቱ አንደኛው መንስኤ ነው።
ሎስ ቼኔሮስ የተባለው ታዋቂ የወንበዴ ቡድን መሪ በሳምንቱ መጨረሻ ከእስርቤት ማምለጡና ከ130 በላይ የእስርቤት ጠባቂዎች ታግተው በርካቶች ከእስር ማምለጣቸውም የወንበዴ ቡድኖቹ ለአዲሱ ፕሬዝዳንት ውሳኔ የሰጡት ምላሽ ተደርጎ ተወስዷል።
በአደንዛዥ እጽ ዝውውር እና ሌሎች ህገወጥ እንቅስቃሴዎች ላይ የተሰማሩ በርካታ የወንበዴ ቡድኖች ያሉባት ኢኳዶር ዋና ዋና የወንበዴ ቡድን መሪዎችን ወደ አዲስ ማረሚያ ቤት ለማዛወር ውሳኔ ስታሳልፍ አመጽ ይከሰትባታል።
ከትናንት ጀምሮ በተቀሰቀሰው አመጽም 10 ሰዎች መገደላቸው የተነገረ ሲሆን፥ የወንበዴ ቡድን መሪዎችን ከእስርቤት የማስመለጡ እንቅስቃሴም መቀጠሉ ተገልጿል።
አመጽና ሁከቱ ፔሩ ከኢኳዶር የሚያዋስትናት ድንበር ላይ ቁጥጥሩ እንዲጠናከር ውሳኔ አሳልፋለች፤ ብራዚል፣ ኮሎምቢያ እና ቺሊ ደግሞ ለኢኳዶር መንግስት ያላቸውን አጋርነት ገልጸዋል።
ኢኳዶራውያን ከሰሞኑ የተከሰቱ ሁነቶችን በማንሳት የፕሬዝዳንት ዳኔል ኖቦአ መንግስት የወንበዴ ቡድኖችን እንቅስቃሴ የመቆጣጠር አቅሙን ጥያቄ ውስጥ ማስገባት ጀምረዋል።
በሀገሪቱ በ2023 በአመጾች ምክንያት ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ከ2022ቱ በእጥፍ ጨምሮ ከ8 ሺህ በላይ እንደነበር በመጥቀስም የፕሬዝዳንት ኖባኦ አስተዳደር የቤት ስራ ከባድ መሆኑን እየገለጹ ነው።